የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ስራ ጀመረ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በይፋ ስራ ጀመረ።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ እና የፈንዱ የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ሰለሞን ደስታ የመድን ፈንዱ ስራ መጀመርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ሰለሞን ደስታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የፈንዱ ስራ መጀመር ለዘርፉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ከለውጡ በኋላ በፋይናንስ ዘርፉ ሪፎርም ከተገኙ ስኬቶች መካከል የሚጠቀስ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ በበኩላቸው በተያዘው በጀት ዓመት 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው እስከ አሁን በፈንዱ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ለፈንዱ ስራ ማስጀመሪያ 25 ሚሊዮን ብር መልቀቁንና የዓለም ባንክ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።
እያንዳንዱ ገንዘብ አስቀማጭ ዋስትና እንዳለው ለማሳወቅ የግንዛቤ መፍጠር ስራ በስፋት ይከናወናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ (Deposit Insurance) ለማቋቋምና ለማስተዳደር የወጣው ረቂቅ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2013 ዓ.ም ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
ፈንዱን ማቋቋም ያስፈለገው በኢትዮጵያ ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገት የአገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት ጤናማ፣ ለአደጋ ያልተጋለጠና የተረጋጋ በማድረግና ለማጠናከር እንዲቻል መሆኑ በደንቡ ተመላክቷል።
በደንቡ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፈንዱን በበላይነት የሚመሩት አምስት የቦርድ አባላትን መሾማቸው ይታወቃል።
ፈንዱ በንግድ ባንኮችም ሆነ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ለሚቆጥበው ወይም ለሚያስቀምጠው ማኅብረሰብ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን፣ በባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ አደጋ ቢያጋጥም፣ አስቀማጮች ካሳ የሚያገኙበት ስርዓት ነው።
የፈንዱ ገንዘብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚከፈት ሂሳብ ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን፣ ሁሉም አባል የፋይናንስ ተቋማት በፈንዱ የሚወሰነውን መነሻ የዓረቦን ክፍያ ወደ ፈንዱ ሂሳብ ገቢ ያደርጋሉ።
መንግሥትም መነሻ ካፒታል እንዲሆን ለፈንዱ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር እንደሚመድብ ደንቡ ደንግጓል።
ፈንዱ የተለያዩ የሀብት መሰብሰቢያ መንገዶችን መጠቀም እንደሚችል በደንቡ ውስጥ የተደነገገ ሲሆን፣ የዓረቦን ክፍያዎችን ከአባል የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ መዋጮዎችን እንደ መንግስትና የልማት አጋሮች ካሉ ሌሎች ምንጮች መሰብሰብና ወደ ራሱ ገቢ ማድረግ እንደሚችል ስልጣን ተሰጥቶታል።