ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረት የኢኮኖሚ ልማትን በዘላቂነት ለመገንባት የሚያስችል ትብብር እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ የውጭ ገበያ በማፈላለግ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ጥሩ መሰረት መጣሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም ባለፉት ሶስት ወራት የፖለቲካ ዲፕሎማሲው ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ጥሩ መሰረት ስለመጣሉ አብራርተዋል። 

የፖለቲካ ዲፕሎማሲው ለምርቶች የውጭ ገበያ ዕድል በማመቻቸት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት መቻሉን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያሳዩ 48 የማስተዋወቂያ መድረኮች በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረት የኢኮኖሚ ልማትን በዘላቂነት ለመገንባት የሚያስችል ትብብር እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት 53 የውጭ ባለሀብቶች የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝትና ምልከታ ማድረጋቸውንም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል። 

አምስት የውጭ ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና ለመስራት መነጋገራቸውን አስታውሰው አሁን ላይ የንግድና ቢዝነስ እንቅስቃሴው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የተደረገው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ያነቃቃ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም እንዲሰፍን እና የጋራ ልማት እንዲጠናከር እየሰራች መሆኑን የገለጹት አምባሳደር መለስ፤ በቀጣናው ያላትን ዲፕሎማሲ ተፅዕኖ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም