የቻይና-ኢትዮጵያ የምርምር ላብራቶሪን በአዲስ አበባ መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና-ኢትዮጵያ የምርምር ላብራቶሪን በአዲስ አበባ መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ) ፡- የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቻይናዋ ሄናን ግዛት ጋር የቻይና-ኢትዮጵያ የምርምር ላብራቶሪ በአዲስ አበባ መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱ በቤልት ኤንድ ሮድ ማእቀፍ መሰረት አብሮ ለመስራት እና የቻይና-ኢትዮጵያ የምርምር ላብራቶሪ መገንባት የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል።
ስምምነቱን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች እና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው በተገኙበት ከግዛቲቱ የስራ ሀላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል።
በተጨማሪም በግዛቲቱ የሚገኘውን ጀንጁ ኖርማል ዩኒቨርሲቲ እና ለዩኒቨርሲቲው ተጠሪ የሆኑ የመጀመርያ ደረጃ እና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶችን መጎብኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ስምምነቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በቻይና በተዘጋጀው አለም አቀፍ የሴቶች ፎረም ላይ በተሳተፉበት ወቅት በሄናን ግዛት ባደረጉት ጉብኝት ከግዛቲቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት የተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል።