የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ዋነኛ መሰረት አድርጎ በመያዝ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ዋነኛ መሰረት አድርጎ በመያዝ መስራት ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የምጣኔ ሃብት ዕድገቱ ዋነኛ መሰረት አድርጎ በመውሰድ በልዩ ትኩረትና ትብብርና መስራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ፈተናዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በንቅናቄው የአገር ውስጥ ምርቶች ገበያ ላይ የተሻለ መነቃቃት የተፈጠረ ሲሆን በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየትና መፍትሄ በመስጠት በኩል አበረታች ጅምሮች መኖራቸው ተነስቷል።
የፌዴራልና የክልል መንግስታት በንቅናቄው ያደረጉት ተሳትፎ አበረታች ቢሆንም ዘርፉ ተወዳዳሪና ለብዙ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንዲችል የበለጠ ጥረት ማዳረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደመቀ መኮንን፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅንጅት መፍታት ያስቻለና ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።
የስትሪንግ ኮሚቴው ለንቅናቄው ስኬት ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን ጠቅሰው በየደረጃው ያለው አመራር ለሚያጋጥሙ ችግሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በቁርጠኝነት መስራት አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የምጣኔ ሃብት ዕድገቱ ዋነኛ መሰረት አድርጎ በመያዝ በላቀ ትብብርና ጥረት መስራት ይገባልም ነው ያሉት።
ከፖሊሲና አሰራር ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅንጅት መፍታት ለነገ የማይባል ተግባር ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።