ቀጥታ፡

አቶ አደም ፋራህ በጅቡቲ ኦልድ ፖርት ተገኝተው የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን አበሰሩ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በጅቡቲ ኦልድ ፖርት (ኤስ.ዲ.ቲቪ ወደብ) ተገኝተው የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን በይፋ አብስረዋል። 

በማብሰሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሣ፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፣ የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለስልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ፣  በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።   

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ለ2016/2017 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።   


 

ለአብነትም የበጋ መስኖናና የመኸር ወቅት ሰብል ልማት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን ምላሽ ለመስጠት ጅቡቲ ወደብ ተገኝተው ወደ አገር ቤት የማጓጓዝ ስራውን አብስረዋል።  

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ለ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ከግዥ ጀምሮ እስከ ማጓጓዝ ባለው ሂደት ጠንካራ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

ለ2016/17 ምርት ዘመን 23 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ለማቅረብ እየሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከዚህ ውስጥም የ13 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም የማጓጓዝ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።   

ካለፈው ዓመት የምርት ዘመን ጋር ሲነፃጸርም በ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያን በብዛት፣ በአነስተኛ ዋጋ እና በጥራት መግዛት እንደተቻለ አስታውቀዋል።   

ግዥ የተፈጸመበትን የአፈር ማዳበሪያም በተሳለጠ መንገድ በማጓጓዝ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ በማድረስ ምርታማነትን የበለጠ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።   

በዛሬው ዕለትም የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራው በይፋ መጀመሩን በመጠቆም፤ በወደብና ማጓጓዝ የስራ ሂደቱ ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ለሚገኘው በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምስጋና አቅርበዋል።   

በግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልዑካን ቡድን የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪ የማጓጓዝ ሂደትን ለመጎብኘት ትናንት ምሽት ጅቡቲ መግባቱ የሚታወስ ነው።

ልዑካን ቡድኑ ጅቡቲ አምቡሊ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለስልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ እና በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም