ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለተውጣጡ ተባባሪ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለተውጣጡ ተባባሪ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ጀመረ
ሆሳዕና፤ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለተውጣጡ ተባባሪ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ዛሬ በሆሳዕና ከተማ መስጠት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ አባላትን ለመመልመል ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት ነው ስልጠናውን እየሰጠ የሚገኘው።
በስልጠና መድረኩም በክልሉ ከሚገኙ ሲቪክ ማህበራት ምክር ቤት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ከሀይማኖት ተቋማት የተውጣጡ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በተጨማሪም ለዕድሮች ማህበራት ጥምረት፣ ለመምህራን ማህበርና ሁሉንም ወረዳና ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ለሚወክሉ ዳኞችን ጨምሮ ከ574 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ስልጠናው እየተሰጠ ይገኛል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ አጎ፣ ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬን ጨምሮ ሌሎች ተገኝተዋል።