የጃፓኑ ቶፓን ሆልዲንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ የህትመት፣ ፓኬጂንግና ዲጂታል ዘርፍ ሊሰማራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጃፓኑ ቶፓን ሆልዲንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ የህትመት፣ ፓኬጂንግና ዲጂታል ዘርፍ ሊሰማራ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ) ፡- የጃፓኑ ቶፓን ሆልዲንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ የህትመት፣ ፓኬጂንግና ዲጂታል አሰራር እንዲዘምን ለማገዝና በዘርፉ መዋዕለ-ነዋይ ለማፍሰስ እየሰራ ይገኛል።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ከኩባንያው የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱም ኩባንያው የሚታወቅበትን የሴኩሪቲ ID፣ ፓስፖርት ህትመት፣ ፓኬጂንግና በዲጂታል ዘርፉ ያለውን ልምድ እና ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ለማሸጋገር የተጀመረውን ሂደት ለማፋጠን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የህትመት፣ ፓኬጂንግና ዲጂታል አሰራር ፍላጎት የኩባንያው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ በህትመት፣ ፓኬጂንግና ዲጂታል ዘርፍ ለመሰማራት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አበረታተዋል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ዕድገት ለማፋጠንና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሚናቸው የጎላ መሆኑን አምባሳደር ዳባ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ኩባንያው በኢትዮጵያ የሚያደርገው የኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ተሳትፎ ወደ ሌሎች አገሮች ለሚያደርገው የስራ እንቅስቃሴ እንደሚያግዘውም ነው ያስረዱት።
የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ኩባንያው የህትመት፣ ፓኬጂንግና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማሸጋገር እና ኢንቨስትመንታቸውን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት በተጀመረው ሂደት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው በሌሎች ዘርፎችም በኢትዮጵያ ለመሰማራት እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል።
የኩባንያው አካል የሆነው ቶፓን ግራቪቲ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር በሽርክና ለመስራት የተስማማ ሲሆን በቀጣይ ወራት ዝርዝር ኮንትራት ከተፈራረሙ በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባ በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል።