ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያሳዩ መድረኮች በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ ተካሂደዋል 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 22/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ የውጭ ገበያ በማፈላለግ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ለኢኮኖሚው ዲፕሎማሲ መሰረት መጣሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም ባለፉት ሶስት ወራት የፖለቲካ ዲፕሎማሲው ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው መሰረት ስለመጣሉ አብራርተዋል። 

የፖለቲካ ዲፕሎማሲው ለኢትዮጵያ ምርቶች የውጭ ገበያ ዕድል በማመቻቸት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት መቻሉን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያሳዩ 48 የማስተዋወቂያ መድረኮች በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ መካሄዳቸውን ተናግረዋል። 

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት 53 የውጭ ባለሀብቶች የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝትና ምልከታ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል። 

አምስት የውጭ ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና ለመስራት መነጋገራቸውን ያስታወሱት አምባሳደር መለስ፣ አሁን ላይ የንግድና ቢዝነስ እንቅስቃሴው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም