በዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ቡድን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን ለመጎብኘት ጅቡቲ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ቡድን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን ለመጎብኘት ጅቡቲ ገባ
ጅቡቲ ፤ ጥቅምት 21/2016 (ኢዜአ)፦ በግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልዑካን ቡድን የ2016/17 ዓ.ም በጀት ዓመት የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን ለመጎብኘት ጅቡቲ ገብቷል።
ኢትዮጵያ ለግብርናው ምርታማነት በሰጠችው ልዩ ትኩረት ከፍተኛ መጠን ያለው የአፈር ማዳበሪያ በተሳለጠ መንገድ ተደራሽ እንዲሆን በከፍተኛ የልዑካን ቡድን ደረጃ ጉብኝት መደረጉ በታሪካዊነቱ ይጠቀሣል።
የልዑካን ቡድኑ ጅቡቲ አምቡሊ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የጅቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለስልጣን ሊቀመንበር አቦበከር ዑመር ሀዲ እና በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውለታል።
በልዑካን ቡድኑም የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሣ፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ ጨምሮ የግብር ሚኒስቴርና የሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የ2016/17 የምርት ዘመን ወደ አገር ውስጥ ከሚገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 51ሺ 420 ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጅቡቲ ወደብ መድረሷን የግብርና ሚኒስትር ማሳወቁ ይታወሳል።
በግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ቡድንም ጅቡቲ የደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን በወደብ በመገኘት ምልከታ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።