የተቋማት አመራሮች ሙስናን የመከላከል ሥራዎች በግንባር ቀደምትነት ሊመሩት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የተቋማት አመራሮች ሙስናን የመከላከል ሥራዎች በግንባር ቀደምትነት ሊመሩት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2016(ኢዜአ)፦ የጸረ-ሙስና ትግሉ ፍሬያማ ለማድረግ የተቋማት አመራሮች የሚጠበቅባቸውን የመሪነት ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ "ሥነ-ምግባራዊ አመራር" በሚል መሪ ኃሳብ ለመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ዘርፍ አመራሮችና ሲቪል ሰራተኞች የሁለት ቀን ሥልጠና ዛሬ መስጠት ጀምሯል።
ሥልጠናው ከባህር ኃይል፣ ሎጂስቲክስ፣ ጠቅላላ አገልግሎትና ሰው ኃብት እንዲሁም መከላከያ መሃንዲስ ጽህፈት ቤት ለተወጣጡ ከፍተኛ መኮንኖችና ሲቪል ሰራተኞች እየተሰጠ ነው።
የሥልጠናው ዓላማም ከፍተኛ መኮንኖች ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የሚጸየፍ አመራር መስጠት፣ በሥራቸው ያሉ ሰራተኞችን ማስገንዘብና ሙስናን የመከላከል ሥራውን ማጠናከር ነው።
በሥልጠናው ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መነሻ ሃሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኢፌዴሪ የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ሥልጠና መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዳግም አላምረው በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ሙስናን ለመከላከል የሙስና ተጋላጭነት ጥናቶችን በማድረግ የመከላከል ሥራዎች ላይ በስፋት እየሰራ ነው።
ከጥናቱ ጎን ለጎን ተቋማት ሙስናንና ብልሹ አሰራር ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው በፍትህ ዘርፍ፣ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ ሥራና ክህሎት ዘርፎች ሥልጠናዎች መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
በመከላከያ ሚኒስቴርም ዛሬ የተጀመረው ሥልጠና የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው የተቋማት አመራሮች ሙስናን በመከላከል ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።
ሥነ-ምግባራዊ አመራር ሥልጠናው በሌሎች ተቋማትም በተጠናከረ መልኩ የሚሰጥ መሆኑንም ነው መሪ ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት።
በመከላከያ ሚኒስቴር የሥነ-ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል አሰፋ ደበሌ በበኩላቸው ሰራዊቱ የአገር ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ የሚያስመዘግበውን አመርቂ ውጤት ሙስናን በመዋጋት በኩልም ሊደግመው ይገባል።
"አገር ከኛ ብዙ ትጠብቃለች" ያሉት ኮሎኔል አሰፋ የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች ያሉ ውስን ኃብቶችን በአግባቡ በመጠቀም፣ ራስን ከብልሹ አሰራሮች በማራቅና አባሎችን በማስገንዘብ ረገድ ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በተቋም ደረጃ የሙስና መከላከል ሥራዎች የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከጸረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር የተጣጣመ መመሪያ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ለዚህም በጥናት ቡድን በኩል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በሥልጠናው የተሳተፉ ከፍተኛ መኮንኖች በበኩላቸው ከሥልጠናው በሚያገኙት እውቀት አባላትን በማሳተፍ ሙስናን መከላከል ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የባህር ኃይል ፋይናንስ ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል ሃብታሙ እሸቱ በበኩላቸው፤ የሠራዊቱ አባላት ሕግና ሥርዓትን ተከትለው ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የበኩሌን እወጣለው ብለዋል።
ሙስናን የመከላከል ሥራ ተጨባጭ የተግባር ሥራ ይጠይቃል፤ ለዛም በቁርጠኝነት እሰራለው ያሉት ደግሞ የመከላከያ መሃንዲስ ጽህፈት ቤት ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው አያሌው ናቸው።