በአዲስ አበባ ኅብረተሰቡን ያሳተፉ ሠላምና ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ኅብረተሰቡን ያሳተፉ ሠላምና ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2016(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ወንጀሎችንና ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ስኬታማ ሥራዎች ተጠናከረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮና የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ አንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ ክንውን በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የቢሮ ኃላፊዋ ሊዲያ ግርማ፤ በመዲናዋ ባለፉት ሦስት ወራት አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች ልዩ ልዩ ወንጀሎችን በመፈጸም የከተማዋን ሰላም ለማደፍርስ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።
ቢሮውም የከተማዋ ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ብሎም ሕገ ወጥ ድርጊትን ለመፈፀም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎችን ለመከላከል ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ከኅብረተሰቡም ጋር በተሰራው ሥራ በመዲናዋ ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎች፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር እንዲሁም ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን መከላከል መቻሉን ነው ያስረዱት።
ወንጀለኞች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።
በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ በመዲናዋ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በተከናወኑ ሠላምና ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የእቅድና በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ሰለሞን ማሞ፤ ባለፉት ወራት በመዲናዋ ወንጀሎችንና ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የተሰሩ ሥራዎች ስኬታማ ነበሩ ብለዋል።
በዚህም የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በሕገ-ወጥ መልኩ ተከማችተው መገኘታቸውን ጠቁመው ወንጀለኞቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በርካታ የኢትዮጵያ ብርና የውጭ አገራት ገንዘቦች ሊዘዋወሩ ሲሉ መያዛቸውን ጠቁመው ጎን ለጎንም ሃሰተኛ የብር ኖቶችም መገኘታቸውን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው በመዲናዋ የደንብ ጥሰቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
በከተማዋ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ግንባታና ሕገ-ወጥ የመሬት ማስፋፋት ተጠቃሽ የደንብ ጥሰቶች መሆናቸው ጠቅሰው እነዚህን ሕገ-ወጥ ተግባራት የመከላከል ሥራ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።
በከተማዋ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ደርጊቶችን በመከላከል ረገድ አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው ባለሥልጣኑ የሚያደርገውን ቁጥጥር ያጠናክራል ብለዋል።