በጋምቤላ የወርቅ ሀብቱን በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል-አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ የወርቅ ሀብቱን በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል-አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ፤ ጥቅምት 21/2016 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰፊ የወርቅ ሀብት በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ።
በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት 63 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ገልጿል።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት የ2016 በጀት ዓመት የሦስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸመን የሚገመግም መድረክ በአኝዋህ ዞን ዲማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በእዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ህገወጥ የወርቅ ዝውውርን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ሀብቱን በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተለይ በኮንትሮባንድ የሚዘዋወረውን ወርቅ ለማስቀረት ከክልል እስከ ቀበሌ የተቋቋመውን ግብረ ኃይል ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ኡሞድ አስገንዝበዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣ የክልሉ መንግስት የወርቅ ማዕድን ልማትን በማዘመን ሀብቱ ለክልሉ ብሎም ለሀገር ልማት እንዲውል በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
መድረኩ እንደ ክልል የተከናወኑ ሥራዎችን ከመገምገም ባለፈ እየቀነሰ የመጣውን የወርቅ ምርት መጠን ምክንያቶች ለመለየትና ለቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አኳታ ቻም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፣ በበጀት ዓመቱ ከክልሉ አራት ወርቅ አምራች ወረዳዎች የተመረተው ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ተልኳል።
"በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከእነዚህ ወረዳዎች 312 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ቢታቀድም ማስገባት የተቻለው 63 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም ብቻ ነው" ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ የተገኘው የወርቅ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ31 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ብልጫ ቢኖረውም ከቀዳሚዎች ዓመታት አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም በዋናነት ህገወጥ የወርቅ ዝውውሩ እየተበራከተ መምጣት ምክንያት መሆኑንና ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ዳይሬክተሯ የገለጹት።
በመሆኑም የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን ለመግታት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር መጠናከር እንዳለበት ወይዘሮ አኳታ ተናግረዋል።