የሞርካ-ግርጫ-ጨንቻ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የሞርካ-ግርጫ-ጨንቻ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ 60 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ። 

72 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የዚህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በቤጂንግ ኧርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ በተሰኘው የሥራ ተቋራጭ እየተከናወነ ነው።

የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ እያከናወነው ይገኛል።

የመንገድ ግንባታው በወረዳ 21 ነጥብ 5 ሜትር፣ በገጠር ከተሞች 12 ሜትር እንዲሁም በገጠር 8 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ በመከናወን ላይ ይገኛል።

የመንገድ ግንባታው ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ ሲሆን ወጪው ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግሥት ተሸፍኗል ተብሏል።  

ግንባታውን በሦስት ዓመት ተኩል ለማጠናቀቅ ታቅዶ በ2011 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዲዛይን ለውጥና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ግንባታውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ አልተቻለም።

ለዚህም ተጨማሪ ፕሮጀክቱ የማጠናቀቂያ ጊዜ ተጨምሮለታል ተብሏል። 

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሶዶ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተመስገን አሸናፊ፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ አፈጻጸሙ 60 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

አሁን ላይ 33 ኪሎ ሜትር አስፋልት የማልበስ ሥራና የ2 ድልድዮች ግንባታ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።  

ጎን ለጎንም የሰብቤዝ፣ የቤዝኮርስ፣ የአፈር ቆረጣና ሙሌት፣ የውኃ መፋሰሻ ቱቦና የፉካዎች ግንባታ ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሬት መንሸራተት ምክንያት ፕሮጀክቱን ለሁለት ከፍሎ የነበረውን የመንገዱ ክፍል ችግሩ እንዲጠና በማድረግ፣ ዲዛይን ተቀርጾ ወደ ትግበራ መግባቱንም ተናግረዋል።

በተለይም የወሰን ማስከበር ችግሮች በግንባታው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ገልጸዋል።

ይህንንም ለመፍታት ተቀራርቦ በመሥራትና የዲዛይን አማራጭ በመፍጠር ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኮር ኮንሰልቲንግ የፕሮጀክቱ አማካሪና ተጠሪ መሃንዲስ አስቻለው ባልቻ በበኩላቸው ኮንትራክተሩ በሙሉ የመፈጸም አቅም ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህንንም የሚያከናውኑ ማሽነሪዎች ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን እንዲሁ። 

አሁንም ለሥራው እንቅፋት የሆነው ከወሰን ማስከበር ጋር ያሉ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸው የሚመለከታቸው አካላት እርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።


 

ፕሮጀክቱን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የቤጂንግ ኧርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ቺፍ ኢንጅነር ጉ ሊን ፒንግ ናቸው።

ፕሮጀክቱ 600 ለሚሆኑ የአካባቢው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥራ እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በዋናነት ሞርካ፣ ዋጫ፣ ወይዛ፣ ሁሉ ቆዴና መሰል ከተሞችን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ያገናኛል። 

መንገዱ ቀደም ሲል ይወስድ የነበረውን የጉዞ ጊዜ በ2 ሰዓት ተኩል እንደሚያሳጥረውም ተነስቷል።

በተጨማሪም በሥፍራው በስፋት የሚመረቱትን የአፕል፣ የድንች፣ የባቄላና ካሮት የመሳሰሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ውጤቶችን በፍጥነት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ማድረስ ያስችላል ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም