ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ መመልከት አለባቸው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ) ፦ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ ሊያዩት እንደሚገባ አሜሪካዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ አገራት ቀጣናውን በኢኮኖሚ ማልማት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይቶችን ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የባህር በርና ወደቦችን በጋራ በመልማት እሳቤ መጠቀም እንደምትፈልግና ይህንንም እውን ለማድረግ በሰጥቶ መቀበል መርህ ሰላማዊ መንገዶችን እንደምትከተል መግለጻቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው መልክዐ ምድራዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮችን በማንሳት በጉዳዩ ላይ ንግግር ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አሜሪካዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ ህጋዊና ፍትሃዊነትን እንዲሁም በጋራ መልማትን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል። 

በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ለሆነችው አገር የወጪና ገቢ ንግድ እድገት ብቻ በማሰብ የተነሳ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣናው አገራት ልማትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በሮችን የመጠቀም ፍላጎትና መሻት ተገቢነት ያለውና የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ የኢኮኖሚ እድገትን ለመጨመር አስተዋጽኦ አለው ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን ለማጤንና ለመመዘን የሚያስችል ውይይት ማድረግ መጀመር አለባቸው ብለዋል።

በመሆኑም የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን የባህር ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ መገንዘብ አለባቸው ሲሉም ነው የተናገሩት። 

በባህር በር ብቻ ሳይገደብ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ በርካታ ወደቦችን ቀጣናዊ የኢኮኖሚ እድገት አካሄድን ተከትሎ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታም ከግምት ያስገባ ምክክር ቢያደርጉ መልካም መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ያነሷቸው የሰጥቶ መቀበል አማራጮች ምክንያታዊና በርካታ ሚሊዮን ሕዝብ ላላት አገር የኢኮኖሚ እድገት ጥያቄ ሚዛን የሚደፋ መሆኑንም አንስተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አገራት ለጋራ አላማዎቻቸው በትብብር ሊሰሩበት የማይችል ምንም አይነት ምክንያት የለም ያሉት ተንታኙ የአገራት መሪዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ቀጣናውን በኢኮኖሚ ማልማት በሚቻልባቸው ሁኔታ ላይ መነጋገር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ከዚህም ባለፈ የባህር በር አማራጭና ወደቦች አጠቃቀም ላይ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ተነጋግረው የመፍትሔ ሀሳቦችን ማፍለቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

 

 

 

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም