የአዲስ አበባ እና የቹንቺን ከተማ እህትማማችነትና የትብብር ግንኙነት በደም ጭምር የተሳሰረ ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ እና የቹንቺን ከተማ እህትማማችነትና የትብብር ግንኙነት በደም ጭምር የተሳሰረ ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ እና የኮሪያ ሪፐብሊኳ ቹንቺን ከተማ እህትማማችነትና የትብብር ግንኙነት በደም ጭምር የተሳሰረ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያውያን ጀግኖች የኮሪያ ሪፐብሊክን የነፃነት ትግል ለማገዝ በዘመቱባት ቹንቺን ከተማ ለመታሰቢያነት ለቆመው ሃውልትና ለተሰጠው ታላቅ ክብርም ከንቲባዋ አመስግነዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ከኮርያ ሪፐብሊክ ቹንቺን ከተማ ከንቲባ ዮክ ዶንግ ሀን ጋር ተወያይተዋል።
ለልዑኩ በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች በተመለከተ ገለፃ የተደረገለት ሲሆን ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ከ2 ሺህ በላይ የተለያዩ መፅሐፍት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በኢትዮጵያና በኮርያ ሪፐብሊክ ቹንቺን ከተማ መካከል ከ60 ዓመታት በላይ የዘለቀው የሁለትዮሽ ግንኙነት በደም የተሳሰረ ነው።
ኢትዮጵያ ለኮርያ ሪፐብሊክ ዜጎች ሁለተኛ ቤታቸው እንደሆነች ገልጸው በሁለቱ አገራት መካካል ያለው የረጅም ዘመን ወዳጅነት በከተሞች መካከል ያለውን ትብብር እንዲቀላጠፍ አድርጓል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ከ24 የተለያዩ አገራት ጋር ያላትን እህትማማችነት ለማጠናከር ተፈራርማ በጋራ እየሰራች መሆኑን አስታውሰዋል።
ቹንቺን ከተማ ጀግኖች የኢትዮጵያ አርብኞች ለኮሪያ ሪፐብሊክ ነፃነት ውድ ዋጋ የከፈሉባት ቦታ መሆኗን አስታውሰው፤ የከተማዋ አስተዳደር አርበኞችን ለመዘከር ያከናወናቸውን ተግባራም አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኮርያ ሪፐብሊክ ነፃነት ወቅት ወታደሮቿን ያዘመተች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር መሆኗን ጠቁመው፣ የኢትዮጵያን ውለታ አስታወሰው በቹንቺን ከተማ ላሰሩት የጀግኖች መታሰቢያ ሀውልት ምስጋና አቅርበዋል።
ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያን ባህልና እሴት የሚያንፀባርቁ ቦታዎችን በመሰየም በሁለቱ ከተሞች መካከል ጠንካራ ትብብር እንዲፈጠር አድርገዋል ብለዋል።
ለኮርያ ሪፐብሊክ ነፃነት የዘመቱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለሁለቱ አገራትና ከተሞች ጠንካራ ትብብር መሰረት መጣላቸውንም አስታውሰዋል።
አዲስ አበባ የዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ክዋኔዎች የሚስተናገዱባት፣ እንደ ቹንቺን ካሉ የኮርያ ሪፐብሊክ ከተሞች ጋር በትብብር የምትሰራ መዲና ነች ብለዋል።
በአዲስ አበባና በኮርያ ሪፐብሊክ ቹንቺን ከተማ መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀው እህትማማችነት ጠንካራ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የልማት ትብብር እንዲኖር ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በኮርያ ሪፐብሊክ የቹንቺን ከተማ ከንቲባ ዮክ ዶንግ ሀን፤ ኢትዮጵያ ለኮርያ ሪፐብሊክ ወዳጅ አገር መሆኗን የማውቀው ገና የአስር ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር ሲሉም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የአይበገሬነት ምልክት የሆነች አገር መሆኗንም ገልጸዋል።
በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለው የስራ ላይ ስልጠና፣ የአደጋ መከላከያ፣ የቴክኖሎጂ፣ የባህል ልውውጥ ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ በኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ የህዝብ ለህዝብና ከተማ ልማት ግንኙነት በደም የተሳሰረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ የሁለትዮሽ ትብብሩ በትምህርት እድል፣ በከተሞች ልማት እና በተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡