አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ለማድረግ የቱሪዝም ሃብቶችን በጋራ ማልማትና ማስተዋወቅ አለብን- ዶክተር ሂሩት ካሣው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ለማድረግ የቱሪዝም ሃብቶችን በጋራ ማልማትና ማስተዋወቅ አለብን- ዶክተር ሂሩት ካሣው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ) ፦ አዲስ አበባን የዓለም ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ለማድረግ እምቅ የቱሪዝም ሃብቶችን በጋራ ማልማትና ማስተዋወቅ አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሣው ገለጹ።
የዓለም የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ ለ36ኛ ጊዜ ''ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት - አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ጀምሯል።
በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ክብረ በዓሉ በይፋ ተከፍቷል።
የበዓሉን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሣው፤ በከተማዋ የሚገኙ እምቅ የቱሪዝም ሃብቶቻችን የሃብት ምንጭ ለማድረግ በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።
አዲስ አበባን የዓለም ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ለማድረግ እምቅ የቱሪዝም ሃብቶችን በጋራ ማልማትና ማስተዋወቅ የጋራ ስራችን ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።
በመዲናዋ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ረገድ በመንግስት እየተደረገ ያለው ከፍተኛ ጥረት እንዳለ ሆኖ በተለይም ከባለሃብቱ ጠንካራ ተሳትፎ ይጠበቃል ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ ለቱሪዝም ልማት ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን ጠቅሰው በቀጣይም ዘርፉን ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፤ የቱሪዝም ዘርፋን በማልማትና በስፋት በማስተዋወቅ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ለማድረግ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
በአገር ውስጥ ያሉ እምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ወደ ቱሪዝም ሃብትነት መቀየር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለ44ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።