ቀጥታ፡

ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ከ356 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ) ፦በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት  ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ምርት ከ356 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ምርቶች መካከል የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

በዚህም መሰረት የምርት አቅርቦትና ጥራትን በማስጠበቅ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የገቢ መጠንን ለማሳደግ በመስራት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለሰልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት አፈፃፀም በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በ2016 በጀት ዓመት ከ364 ሺህ ቶን በላይ የቡና፣ የሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 79 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሩብ ዓመቱ 70 ሺህ 480 ቶን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 356 ሚሊየን 900 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከምርቶቹ 429 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገኘበት እንደነበር አስታውሰዋል።

በ2015 ዓ.ም አንደኛ ሩብ ዓመት ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም በድምሩ 75 ሺህ 401 ቶን ለውጭ ገበያ የቀረበ ሲሆን ዘንድሮ በተመሳሳይ ወራት ከ70 ሺህ 480 ቶን በላይ መቅረቡን ገልጸዋል። 

የዓለም ገበያ የቡና መግዛት ፍላጎት መቀዛቀዝ፣ የኑሮ መወደድ፣ የዩክሬን እና የራሽያ ጦርነት ለገበያው መቀዛቀዝ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

የምርት ብዛትን በመጨመርና ጥራትን በማስጠበቅ ማቅረብ እንዲሁም የገበያ መዳራሻዎችን የማስፋት ስራ የሚከናወን መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች መዳረሻ ከሆኑት አገሮች መካከል ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች፣ ሱዳን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ኔዘርላንድ፣ ኬኒያ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም