ለምርት ዘመኑ ከ132 ሺህ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ብዜት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለምርት ዘመኑ ከ132 ሺህ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ብዜት እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ) ፦ ለበጋ የመስኖና ለመጪው መኸር እርሻ በአርዳይታ እና ጎንዴ ኢተያ የምርጥ ዘር ማባዣ ከ132 ሺህ ኩንታል በላይ የሚገመት የምርጥ ዘር ብዜት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ኮርፖሬሽኑ ለዘመናዊ እርሻና ለአግሮ ኢንዱስትሪ መስፋፋት መሠረት የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ በማድረግ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ይታወቃል።
በዚህም ኮርፖሬሽኑ በአርዳይታ፣ ጎንዴ ኢተያ፣ ጊቤ፣ ቻግኒና ታማሻሎ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎች፣ በግል እርሻዎችና በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር አቅርቦት ለመፍታት እየስራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኮርፖሬሽኑ አርዳይታ እና የጎንዴ ኢተያ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች የተመረተው ምርጥ ዘር ለመስኖና ለመኸር እርሻው የሚውል ነው ብለዋል።
በምርት ዘመኑ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ በሽታን መቋቋም የሚችሉ ከ132 ሺህ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ብዜት እየተከናወነ ነው።
የኮርፖሬሽኑ አርዳይታ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ከበደ እንደገለፁት፤ የአርዳይታ ቅርንጫፍ በኮርፖሬሽኑ ከሚገኙ የእርሻ ጣቢያዎች ትልቁና ከ3 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መሬት የሚሸፍን ነው።
በዘንድሮ ምርት ዘመን ቅርንጫፉ ከ82 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ፣ የጎመን ዘርና የገብስ ምርጥ ዘሮችን ለመሰብሰብና ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል።
በኮርፖሬሽኑ የአሰላ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ቀፀላ የጎንዴ ኢተያ የምርጥ ዘር ማባዣ ከምርምር ተቋማት የተገኙ የቅድመ መስራች፣ መስራችና የተመሰከረላቸው ምርጥ ዘሮች በማባዛት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቅርንጫፉ በ10 ሰብሎች 36 ዝርያዎች በማባዛት ላይ እንደሆነ ጠቁመው፤ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሽንብራ፣ ምስር፣ ጎመን ዘር እና ተልባ እንደሚገኙበትም ጠቅሰዋል።
ከጣቢያው በተጨማሪ የግል እርሻዎች እና በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮችን ማሳ በኮንትራት በመውሰድ የምርጥ ዘር የማብዛት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በዘንድሮ ዓመት ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ቅርንጫፎቹ ከህዳር ወር መጀመሪያ ጀምሮ ወደ ምርት መሰብሰብ እንደሚገቡ ተናግረው፤ በምርት አሰባሰብ ወቅት ብክነት እንዳይከሰት የቅድመ ዝግጅት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።