ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተቀናጀ የቱሪዝም አገልግሎት (የቱሪዝም ፓኬጅ) ለጎብኚዎች ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ) ፦አዳዲስና ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን በጋራ ለመጎብኘት የሚያስችል የቱሪዝም ፓኬጅ በመቅረፅ የጎብኚዎችን ቆይታና የቱሪስቶችን ፍሰት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለፀ።   

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች እየለሙ ነው። 


 

ለአብነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኃሳብ አመንጪነት እየተተገበሩ ያሉትን ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለአገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ጠቅሰዋል። 

ጎን ለጎንም ለጎብኚዎች አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ-ልማት ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም ረገድ ፓርኮች በቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የማኅበረሰብ ኢኮ ሎጅና የቱሪዝም መረጃ ማዕከላት ግንባታዎችን በማሳያነት አንስተዋል።

በተጓዳኝም፤ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ሆቴሎች፣ ሎጅና ሪዞርት ግንባታ እያከናወኑ መሆኑንም ገልፀው ይህንን ለማበረታታት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከነባሮቹ ጋር በማስተሳሰር ለዓለም ገበያ የማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። 

አስጎብኚ ድርጅቶች አዳዲሶቹን ከነባሩ ጋር በማስተሳሰር የቱሪዝም ፓኬጆች በዓለም አቀፍ ገበያ በማስተዋወቅ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የሙመንትስ ትራቭል ኤጀንሲ ቱር ኦፕሬተር ጋሻው ጌታሁን፤ የቱሪዝም መዳረሻዎች መጨመር የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘም ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ለማጎልበት ያስችላል ብለዋል።

ይህንንም ከግምት በማስገባት ነባሩንና አዲሱን የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች በማቀናጀት የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ጀስት ፎር ዩ ሥራ አስኪያጅ ሰፊው ኃይለማርያም በበኩላቸው አዳዲስ መዳረሻዎች ሲስፋፉ የቱሪዝም ዘርፉ የበለጠ ተፎካካሪ እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት።


 

በዚህም አሁን ላይ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከነባሮቹ ጎን ለጎን በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ድርጅታቸው እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በ"ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክት ስምንት ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን ለማልማት ገቢ የማሰባሰብ ሥራም እየተከናወነ ነው።   

ፕሮጀክቶቹም በትግራይ ክልል "ገራ አልታ"፣ በኦሮሚያ ክልል "ጅማ" በአማራ ክልል "ሃይቅ" በደቡብ ክልል "አርባ ምንጭ"፣ በአፋርና ሱማሌ ክልሎች እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዳሴ ግድብ አካባቢና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚተገበሩ መሆናቸው  ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በታሪክ፣ ባህልና መልክዓ ምድር የታደለች በርካታ የቱሪስት መስህቦች ያሏት አገር መሆኗ ይታወቃል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗም እንዲሁ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም