ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራሉ 

 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ  የአምስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር  የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና ከሻሸመኔ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በሁለት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፍ በሁለቱ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ሻሸመኔ ከተማ በበኩሉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁሉም የተሸነፈ ሲሆን ያለ ምንም ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ክለቦቹ በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ።

ከምሽቱ 12 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወልቂጤ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ በመውጣት በስምንት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

በ2015 የውድድር ዓመት በመጨረሻው ጨዋታ ከመውረድ የተረፈው ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፍ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

በሁለት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት፤ መቻል ከሀምበሪቾ ዱራሜ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆዩ ይሆናል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም