ሉሲዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬ በአቡጃ አቢዮላ ስታዲየም ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሉሲዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬ በአቡጃ አቢዮላ ስታዲየም ያደርጋሉ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ)፡- በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአፍሪካ ዞን ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር ዛሬ በአቡጃ አቢዮላ ስታዲየም ያደርጋል።
የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ይደረጋል።
ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሳምንት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ለማድረግ ከትናንት በስቲያ ወደ ስፍራው ማምራቱ ይታወቃል።
የመጨረሻ ልምምዱንም ትናንት ጨዋታው በሚደረግበት አቢዮላ ስታዲየም ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በ67 ዓመቱ አሜሪካዊ ራንዲ ዋልድሩም የሚሰለጥነው የናይጄሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ላለፉት ቀናት በአቡጃ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።
አሰልጣኝ ራንዲ ዋልድሩም በአሜሪካ ባለባቸው የግል ጉዳዮች ምክንያት በመጀመሪያ ጨዋታ ቡድናቸውን ሜዳ ተገኝተው ያልመሩ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ቡድናቸው ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቶጎዋዊቷ ኬንዲ ኤዶህ የሁለቱን አገራት ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ጨዋታ ካሸነፈ በቀጣዩ ዙር ከዩጋንዳና ካሜሮን አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል።
ዩጋንዳ በመጀመሪያ ጨዋታ 2 ለ 0 ያሸነፈች ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ዛሬ የሚደረግ ይሆናል።
በአራት ዙር በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ሁለት አገራት አፍሪካን ወክለው በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) አስታውቋል።