ቀጥታ፡

የጤና ሚኒስቴር የጋራ ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ) ፡- የጤና ሚኒስቴር የጋራ ስትሪንግ ኮሚቴ የጤና ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ በባለፈው የጋራ ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተነሱ ውሳኔዎች ክትትል እና ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ዝርዝር ጉዳዮች ቀርበዋል።

በተጨማሪም የ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስ አጠቃቀምን ጨምሮ የጤና ዘርፍ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የዘርፉ ጥቅል አፈፃፀም የተሻለ  ቢሆንም በክልሎች መካከል የአፈፃፀም ልዩነቶች መታየቱ በሪፖርቱ መመላከቱን የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል።


 

የጤናው ዘርፍ የመካከለኛ ጊዜ (የሶስት ዓመት እቅድ) የእድገትና የኢንቨስትመንት እቅድ እና እቅዱን ለማስፈፀም የሚያስፈልገው የገንዘብ ምንጭ፣ እንዲሁም የጤናው ዘርፍ የ2016 በጀት እቅድ በመድረኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታን የሚመለከት በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተደረገ ሃገራዊ የዳሰሳ ጥናትም በመድረኩ ቀርቧል።


 

በውይይቱም በተለይ በጤናው ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎት ጥራት ላይ ይበልጥ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስገንዝበዋል።

ከጥቅምት 21 እስከ 23/ 2016 ዓ.ም 25ኛው አመታዊ የጤና ጉባኤ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም