ቀጥታ፡

የእግር ኳስ ቤተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ  ፤ ጥቅምት 20/2016 (ኢዜአ) ፡-የእግር ኳስ ስቴዲየሞች የፊፋና ካፍን መመዘኛ አሟልተው እንዲገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ስታዲየሞችም ደረጃውን ጠብቀው በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ። 

በአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ  የተካሄደው 15ኛው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።


 

በጉባኤው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮችና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ)፣ የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች፣ የክለብ አሰልጣኞች፣ የዳኞች ተወካዮችና ሌሎች የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ተገኝተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ የካፍን ዝቅተኛ መስፈርቶች የሚያሟሉ ስታዲየሞች ባለመኖራቸው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በሜዳው እንዳያደርግ ማገዱ የሚታወስ ነው።  

ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎችን በተለያዩ አገራት ማድረጉ ፌዴሬሽኑ ለእግር ኳስ ልማትና እድገት ማዋል ያለበትን ገንዘብ ለቡድኑ ወጪ እያደረገ እንደሚገኝና በዚህም ዋጋ እየከፈለ እንደሚገኝ አቶ ኢሳያስ ጅራ ገልጸዋል።

እስከ አሁን ቡድኑ ከአገር ውጪ ላደረጋቸው ጨዋታዎች ፌዴሬሽኑ ከ66 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አመልክተዋል።

መንግሥት የአገር አርማ የሆነውን ብሔራዊ ቡድን በአገሩ እንዲጫወት የጀመራቸውን ሥራዎች በፍጥነት በማጠናቀቅ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። 

በሌላ በኩል እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በታዳጊዎችና ሴቶች የእግር ኳስ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።  

በታዳጊዎች እግር ኳስ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በሁለቱም ጾታዎች ከ15 ዓመት በታች የፓይለት ፕሮጀክት ቀርጾ እየተገበረ ይገኛል ነው ያሉት አቶ ኢሳያስ።

ከሴቶች እግር ኳስ ጋር በተያያዘም  በተሰጠው ትኩረት በተለያዩ እርከኖች እየተካሄዱ ላሉ ውድድሮች የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የክለቦች የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አሰጣጥ በቀጣዩ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ  ተቋርጦ የነበረውና በድጋሚ የተጀመረው የካፍ ሲ እና ዲ ላይሰንስ ስልጠና እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

ፌዴሬሽኑ ለአጠቃላይ እግር ኳስ ልማትና እድገት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በአገሩ የመጫወት ጉዳይ በአጭር ጊዜ እልባት በመስጠት የእግር ኳስ ቤተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በተለየ ሁኔታ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ስታዲየሞች ሲገነቡ የፊፋና ካፍን መመዘኛ እንዲያሟሉ አስፈላጊው ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በተያያዘም የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት የሲቪል ምህንድስናው ሥራ መጠናቀቁንና የሳር ንጣፉ የሚያከናውን ደረጃውን የሚያሟላ ድርጅት በመፈለግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ካላት ታሪክ አንጻር አገሪቷን የሚመጥን ውጤት በዓለምና በአህጉር አቀፍ መድረክ ያላትን ውጤት ማሻሻል ላይ ፌዴሬሽኑ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የጠቅላላ ጉባኤው አባላት እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አሰራሩን ለማዘመንና ከሌሎች አገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር የጀመረው ሥራ አበረታች እንደሆነ ጠቅሰው በእግር ኳስ ልማትና እድገት እንዲሁም በብሔራዊ ቡድኑ ውጤት መሻሻል ላይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

ትናንት ማምሻውን በተደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የማሟያ ምርጫ  ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ92 ድምጽ፣ ኢብራሂም ሙክታር ከአፋር ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ80 ድምጽ እና ማዕረጉ ሀብተማርያም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ76 ድምጽ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በመሆን ተመርጠዋል።

ተመራጮቹ  ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ያገለግላሉ።

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ማሻሻያ ደንብ፣ የፌዴሬሽኑ የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸምና  የ2016 እቅድ ሪፖርት ውይይት ተደርጎበት በጠቅላላ ጉባኤው ፀድቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም