ከአንድ ሚሊየን በላይ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
ከአንድ ሚሊየን በላይ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2016(ኢዜአ)፦የሥራና ክሎት ሚኒስቴር "ሄፈር ኢንተርናሽናል" ከተሰኘው መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ሰነድ ተፈራረመ።
የመግባቢያ ሥምምነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልና በአፍሪካ የሄፈር ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዝዳንት አደሱዋ ኢፊዲ ፈርመውታል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ የሥምምነቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ።
ሥምምነቱ በተለያዩ መስኮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
በሥምምነቱ መሰረት በተለይም እሴት ሰንሰለትን መሰረት ባደረገ የግብርና ሥልጠና ከአንድ ሚሊየን በላይ ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ሥምምነቱ በተለይም የግብርናው ዘርፍ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
በአፍሪካ የሄፈር ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዝዳንት አደሱዋ ኢፊዲ በበኩላቸው ድርጅታቸው የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ድርጅቱ ይህንንም ልምዱን በመጠቀም በኢትዮጵያም ለወጣቶች አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ወጣቶች አቅማቸውን እንዲያወጡና እንዲጠቀሙ የድርሻቸውን እንደሚወጣ ጠቁመዋል።