የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሶስት አዳዲስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መረጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሶስት አዳዲስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መረጠ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የማሟያ ምርጫ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም፣ ኢብራሂም ሙክታርና ማዕረጉ ሀብተማርያም የኮሚቴው አባላት በመሆን ተመርጠዋል።
የፌዴሬሽኑ 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ተካሂዷል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮችና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ተወካዮች፣ የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች፣ የክለብ አሰልጣኞች፣ የዳኞች ተወካዮችና የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ተገኝተዋል።
የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ማሟያ ምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎችን በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
በዚሁ መሰረት አወል አብዱራሂም፣ ሕይወት አረፋይኔ እና አስፋው ፀጋዬ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ኢብራሂም ሙክታር እና አሲያ አብዱልቃድር ከአፋር ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ማዕረጉ ሀብተማርያም፣ ሄለን ደበበና እስራኤል አታሮ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በማሟያ ምርጫው የተሳተፉ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
ከአፋር ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በምርጫው ለመወዳደር ጥያቄ ያቀረቡት አሊሚራህ መሐመድ አሊ ሶስት የምርጫ ዘመን ያገለገሉ በመሆናቸው ኮሚቴው በምርጫ መመሪያው መሰረት ከውድድሩ ውጪ አድርጓቸዋል።
በተካሄደው ምርጫ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ92 ድምጽ፣ ኢብራሂም ሙክታር ከአፋር ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ80 ድምጽ እና ማዕረጉ ሀብተማርያም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ76 ድምጽ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በመሆን ተመርጠዋል።
ተመራጮቹ ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ያገለግላሉ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ዘጠኝ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መምረጡ የሚታወስ ነው።
ይሁንና ጠቅላላ ጉባኤው በተለያዩ ምክንያቶች በሕዳር ወር 2014 ዓ.ም በተመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በትግራይና አፋር ክልሎች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ሳያካሄድ መቅረቱ የሚታወስ ነው።