ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል ከ 8 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል ከ 8 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2016 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ እና አየርላንድ በኢትዮጵያ ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል ከ8 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እና በአየርላንድ የዓለም አቀፍ ልማትና ዳያስፖራ ሚኒስትር ዴኤታ ሲያን ፊሊሚንግ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ ኢትዮጵያና አየርላንድ ለበርካታ አመታት በዘርፈ ብዙ የልማት ትብብሮች በጋራ እየሰሩ እስካሁንም መዝለቃቸውን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም በኢትዮጵያ ለተለያዩ የልማት ትግበራ የሚውል ከ8 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የድጋፍ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።
የድጋፍ ስምምነቱም ለሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ ለጤና ሴክተር ልማት እና የሪፎርም ስራዎችን የሚያስተባብሩ ተቋማትን አቅም ለማጎልበት የሚውል መሆኑን አብራርተዋል።
አየርላንድ የኢትዮጵያ ጠንካራ የልማት አጋር መሆኗን ያነሱት ሚኒስትሩ ባለፉት 20 አመታት ብቻ በኢትዮጵያ የልማት እድገት 200 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ መደረጉን እስታውሰዋል።
በዲፕሎማሲው መስክ አየርላንድን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ የትብብር ግንኙነቷን አጠናክራ መቀጠሏን ገልጸዋል።
በአየር ላንድ የዓለም አቀፍ ልማትና ዳያስፖራ ሚኒስትር ዴኤታ ሲያን ፊሊሚንግ፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የትብብር ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች አየርላንድ አጋዥ በመሆን የምትሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።