የሳይበር ምህዳር ንቃተ ህሊናን ለማጎልበት መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል-ዶክተር ለገሰ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሳይበር ምህዳር ንቃተ ህሊናን ለማጎልበት መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል-ዶክተር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2016 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙኃን የዜጎችን የሳይበር ምህዳር ንቃተ ህሊናን የማጎልበት ኃላፊነት እንዳለባቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።
4ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር "አይበገሬ የሳይበር አቅም ለሀገር ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች መካሄድ ከጀመረ 19 ቀናትን አስቆጥሯል።
በዛሬው ዕለትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና የጥናት ውጤት ይፋ ተደርጓል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የሳይበር ምህዳር ውስብስብና ከግለሰቦች የእለት ከለት ሥራ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
ሳይበር ቀድመው የተዘጋጁ ሀገራትን ሁለንተናዊ እድገት በማረጋገጥ ተጠቃሚ ማድረጉን በመጥቀስ፤ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ በሚፈለገው ልክ ባለማዘጋጀታቸው ለበርካታ ኢ-ተገማች ችግሮች እየዳረገ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ፣ ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ለማሳካት ብሎም የግል ንብረትን ለመጠበቅ የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችል እርምጃ መውሰድ አለብን ነው ያሉት፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገሪቱን ሳይበር ምህዳር በብቃት እየመራ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ በዘርፉ የላቀ እውቀት ያላቸውን ወጣቶች ለማፍራት የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ዜጎች በሳይበር ምህዳር ላይ ያላቸውን ንቃተ ህሊና በማስፋት የኢትዮጵያን የዲጅታል ሉዓላዊነት ማቀላጠፍ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
የሳይበር ጥቃትን መከላከል የዜጎችና የተቋማት የተቀናጀ እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ መገናኛ ብዙኃን ከአንድ ወቅት ዘገባ ወጥተው ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ መፍጠር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ እንዳሉት፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 2 ሺህ 556 የሳይበር ጥቃት ደርሶ 97 ነጥብ 73 በመቶ ማክሸፍ መቻሉን ገልጸው፤ ጥቃቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ ከተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት አይነቶች መካከል የድረገጽ ጥቃት 764 በማስተናገድ ቀዳሚው ሲሆን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በድረገፅ ጥቃት የተሞከረው 258 እንደነበር አስታውሰዋል።
በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሰርጎ በመግባት ሙከራ የደረሰው የሳይበር ጥቃት 138 እንደነበር አስታውሰው፣ ዘንድሮው ሰርጎ በመግባት 669፤ በመሰረተ ልማት ማቋረጥ 590 ጥቃት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በዓለም ዙሪያ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሳይበር ጥቃት የሚደርሰው በተጠቃሚዎች የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ክፍተት መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በመሆኑም የዜጎችን ንቃተ ህሊና የሚያጎለብቱ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መስራት እንደሚገባ ገልጸው፤ በጉዳዩ ላይ ለሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ መገናኛ ብዙኃን ለህብረሰተቡ ስለ ሳይበር ደህንነት ምንነት፤ የሳይበር ጥቃትን መከላከልና ከደረሰ በኋላ እንዴት ማክሸፍ እንዳለባቸው መረጃ በመስጠት የህዝብ አገልጋይነታቸውን ማሳየት አለባቸው ብለዋል፡፡