ቀጥታ፡

ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በልማት ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ነው - ኮሚሸነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2016(ኢዜአ)፦  ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለራስ ፍጆታ የሚሆኑ የግብርና የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ በአቪዬሽን መምሪያ በ70 ሄክታር መሬት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዙሪያ የለማውን የጤፍ ሰብል የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጎብኝተዋል።


 

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የተገነባው የአቪዬሽን መምሪያ ቢሮም ተመርቋል። 

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለራስ ፍጆታ የሚሆኑ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የፖሊስ አባላት ሁሌም ዝግጁ በመሆንና በንቃት በመጠበቅ ለህዝብ ደህንነት የቆሙለትን ዓላማ መወጣቱ እንዳለ ሆኖ በከተሞችም የግብርና ልማት እንዲሳካ እገዛ እያደረጉና ራሳቸውም እያለሙ ነው ብለዋል።

የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ፤ ፖሊስ ወንጀል ከመከላከል በተጓዳኝ በልማት ስራዎችም በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል፣ በግብርና ስራዎች አልሚዎችን በማገዝና በሌሎችም ማህበራዊ ተሳትፎዎች በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በወንጀል መከላከል ዘርፍ የአቪዬሽን መምሪያ ከመደበኛ ስራቸው ባለፈ በግብርና ስራ ላስመዘገቡት ውጤት በከፍተኛ ሃላፊዎቹ ምስጋና ቀርቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም