የደረሰ ሰብል በዝናብ እንዳይበላሽ ፈጥኖ ለመሰብሰብ ርብርብ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የደረሰ ሰብል በዝናብ እንዳይበላሽ ፈጥኖ ለመሰብሰብ ርብርብ ያስፈልጋል
አዳማ፤ ጥቅምት 19/2016(ኢዜአ):-የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ አርሶ አደሩ ኮምባይነርና የሰው ሀይል በስፋት በማሳተፍ ሰብሉን እንዲሰበስብ የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደገለፁት በሀገሪቷ ቆላማና ወይና ደጋ አካባቢዎች የመኸር አዝመራ እየተሰበሰበ ነው።
በተለይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ በሰሜን ምስራቅ አማራና ትግራይ ክልሎች ጤፍ፣ ስንዴ፣ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ የሰሊጥና ማሽላ ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል።
''በአብዛኛው የሀገሪቷ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ ይገኛል'' ያሉት አቶ ኢሳያስ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም ኮምባይነር በመጠቀምና በደቦ የደረሰውን ሰብል በፍጥነት ለማንሳት አርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያው ጥረቱን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።
ኮምባይነሮችን ሰብል ወደ ደረሰበት ዞኖችና ወረዳዎች በማንቀሳቀስ የአጨዳ ተግባር እንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም አርሶ አደሩ ቤተሰቦቹን ጨምሮ የየአካባቢውን የሰው ሃይል በማቀናጀት በደቦ የደረሰውን ሰብል መሰብሰብ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
''ከክልሎች ጋር የጋራ አጀንዳ ፈጥረን በየሳምንቱ የደረሰውን የሰብል አሰባሰብ ሂደት እየገመገምን ተጨማሪ አቅጣጫ እየሰጠን ስራውን በቅንጅት እየመራን ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው በጥቅምት፣ ህዳርና ታህሳስ ወራት ዝናብ እንደሚኖር ባለፈው መስከረም የአየር ጸባይና የዝናብ ሁኔታ ትንበያ መሰጠቱን አስታውስዋል።
በዚህም ባለፈው ዓመት በድርቅ በተጎዱ የደቡብ ቆላማ፣ ደቡብ ምስራቅና ምስራቅ የሀገሪቷ አካባቢዎች ለሰብልና ለእንስሳት መኖ ልማት አመቺ የሆነ ዝናብ እንደሚኖር ተናግረዋል።
በተለይ የበጋ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች፣ የምስራቅ የሶማሌ ክልል አካባቢዎችና የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በቂ ዝናብ ስለሚያገኙ አምና ያጋጠመውን ድርቅ የሚያካክስ ስራ መስራት ይቻላል ብለዋል።
ሰብል አብቃይ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስለሚኖር ህብረተሰቡ በሰብል አሰባሰብ ላይ ጥንቃቄ በማድረግ ሊያጋጥም የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።