ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
በስትራቴጂው መሰረት 96 ዓይነት ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ግብ መያዙንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተኪ ምርት ስትራቴጂ ሰነድ ዙሪያ ከፌዴራል እና ክልል ባለድርሻ አካላት፣ ኢንዱስትሪዎችና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው እና ወደ ውጭ የምትልከው ምርት መጠን አሁንም አልተመጣጠነም።
እንደ ሀገር ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት 18 ቢለዮን ዶላር ስናወጣ ወደ ውጭ የምንልከው ንግድ መጠን ከ4 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ የንግድ ሚዛኑ አለመመጣጠን ማሳያ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ሚኒስትሩ ለንግድ ሚዛኑ አለመጠበቅ ምርትና ምርታማነት በሚጠበቀው ደረጃ አለማደጉ፣ እሴት ያልተጨመረባቸው ምርቶችን ወደ ውጭ መላክና ሌሎችም ችግሮችን በመንስኤነት ጠቅሰዋል።
ወደ ውጭ የሚላከውን እና ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ለማመጣጠን የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት ሰፊ ጥናት መደረጉን ጠቁመው ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ለአንድ ዓመት ያህል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ስትራቴጂው ከውጭ የሚገቡ 96 ምርቶችን በአገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማምረት የሚያስችል ሲሆን ይህም አገሪቷ ያላትን ጥሬ ዕቃ፣ የሰው ሃይል እና ቴክኖሎጂ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ነው የገለጹት።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በስትራቴጂው መሰረት የማምረት አቅም እያደገ ሲሄድ የሚተኩ የምርት ዓይነቶችን የማሳደግ ስራ ይሰራል።
በሌላ በኩል ባለፉት ሶስት ወራት 350 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶች በአገር ውስጥ ማምረት መቻሉን ሚኒስትሩ ትናግረዋል።