የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ጨዋታውን እንዲያደርግ መንግስት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ጨዋታውን እንዲያደርግ መንግስት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን መስፈርቱን በማሟላት በአገሩ ሜዳ ጨዋታውን እንዲያደርግ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መስፍን ቸርነት፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮችና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች፣ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን(ካፍ) ተወካዮች፣ የክለብ አሰልጣኞች፣የዳኞች ተወካዮችና ሌሎች የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ተገኝተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚህ ወቅት፤ እግር ኳስ በኢትዮጵያ ካለው ሕዝባዊ መሰረት ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረክ ለገጽታ ግንባታና በስፖርት ዲፕሎማሲ ከአገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በእግር ኳስ ልማትና ከሌሎች አገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ትብብር ለመፍጠር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ካላት ታሪክ አንጻር አገሪቷን የሚመጥን ውጤት በዓለምና በአህጉር አቀፍ መድረክ ለማስመዝገብ ፌዴሬሽኑ በትኩረት መስራት አለበት ነው ያሉት አምባሳደር መስፍን።
መንግስት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስፈርትን ያሟላ ስታዲየም በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በሜዳው እንዲጫወት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፤ የፊፋ እና ካፍ መስፈርት ያሟላ ስታዲየም በኢትዮጵያ ባለመኖሩ ለእግር ኳስ ልማት መዋል ያለበት ወጪ ለውጭ አገራት ጉዞና ተያያዥ ወጪ እየዋለ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ እንዲያበጅ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በታዳጊዎችና ሴቶች የእግር ኳስ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ አሰራርን ወደ ስራ ለማስገባት እንዲሁም ተቋርጦ የነበረውና በድጋሚ የተጀመረው የካፍ ሲ እና ዲ ላይሰንስ ስልጠና እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
ፌዴሬሽኑ ለአጠቃላይ እግር ኳስ ልማትና እድገት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።
በጉባኤው የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸምና የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የማሟያ ምርጫ እንደሚከናወንም ተጠቁሟል።