ቀጥታ፡

የግብርና ሚኒስቴር ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ተሽከርካሪዎችንና የቤተ-ሙከራ መሳሪያዎችን ለክልሎችና ለምርምር ማዕከል አስረከበ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2016 (ኢዜአ) ፦ የግብርና ሚኒስቴር ከልማት አጋሮች በተገኘ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ የተገዙ ተሽከርካሪዎችንና የቤተ-ሙከራ መሳሪያዎችን ለክልሎችና ለምርምር ማዕከል አስረከበ።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኡስማን ዲዮን፣ የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የክልልና ወረዳ የፕሮግራም አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡ 

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ድጋፉ በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስራዎችን ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ ነው።

እንደ ሀገር በበጋ ስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ ልማትና ሌሎች የግብርና መስኮች  ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የዘርፉ ተቋማት አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ የልማት አጋሮችና ማህበረሰቡ የተቀናጀ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተጀመሩ ተግባራትን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።


 

አብዛኛውን አርሶ አደር ትርፋማ የማምረት ደረጃ ላይ ለማድረስ ቀልጣፋ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡

በዛሬው ዕለትም በ34 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ የገንዘብ ድጋፍ የተገዙ 197 ተሽከርካሪዎች፣ 1 ሺህ 850 ሞተር ሳይክሎችና የቤተ ሙከራ መሳሪያዎች ለክልሎችና ለግብርና ምርምር ማዕከል መሰጠቱን አንስተዋል።

በ"ግብርና ዕድገት ፕሮግራም" ታቅፈው በአዲሱ የምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ላልተካተቱ 53 ወረዳዎችና ወረዳዎቹ ለሚገኙባቸው አስር ክልሎች የተሽከርካሪና የሞተር ሳይክል ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ የማህበረሰብ የተፋሰስ ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አፈጻጸምና የግብርና ምርትን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግስት ከዓለም ባንክ ባገኘው 500 ሚሊዮን ዶላር የገንዘበ ድጋፍ ''በአየር ንብረት አፈጻጸም የመሬት አያያዝ ፕሮግራም’’ ላይ በአስራ አንድ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 501 ወረዳዎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር የማህበረሰብ ተፋሰስን እየተገበረ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመሬት አያያዝ ፕሮግራሙን ተደራሽነት ለማሻሻልም 114 ተሽከርካሪዎችና 1 ሺህ 500 ሞተር ሳይክሎች ለክልል ማስተባበሪያዎችና ለወረዳዎች ርክክብ መደረጉን ነው ያነሱት።

ሚኒስቴሩ የምግብ ስርዓትን ለማሻሻልና በንጥረ ነገር የበለጸጉ የግብርና ምርቶችን በቀላሉ የማምረት ዘይቤን ለማዳበር ከምርምር ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ይህንን ውጤታማ ለማድረግም ከህጻናት አድን ድርጅት በተገኘ 3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ለመልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከል የምግብና የሥነ ምግብ ቤተ ሙከራ መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ርክክብ የተፈጸመባቸው ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ድጋፎች በተለያዩ አጋር አካላት የሚደገፉ ፕሮግራሞችን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡


 

 በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ዳይሬክተር ኡሳማን ዲዮን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ጨምሮ በመሬት አያያዝ ዘርፍ ውጤታማ ስራ እያከናወነች ነው ብለዋል።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን መልካም ተሞክሮ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በተለይም በተፋሰስ የለሙ መሬቶችን በዲጂታል የመረጃ ቋት እንዲመዘገቡና ደህንነታቸው በዘላቂነት እንዲጠበቅ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡


 

 ድጋፍ ከተደረገላቸው ክልሎች መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ መስፍን ወልዱ  የተደረገው ድጋፍ የግብርና ዘርፍን ውጤታማ ለማድረግና ስራዎችን ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

የተደረገላቸውን ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ዝግጁ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም