ቀጥታ፡

ብሔራዊ አርበኝነትን መፍጠር የሚያስችል አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ያስፈልጋል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2016 (ኢዜአ)፦ የተዛቡ ትርክቶችን በማስተካከል ብሔራዊ አርበኝነትን መፍጠር የሚያስችል አሰባሳቢና የጋራ ትርክት መገንባት እንደሚስፈልግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ። 

በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ "ከዕዳ ወደ ምንዳ" በሚል መሪ ሀሳብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።

በዚሁ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ስልጠናው የምክር ቤት አባላት የተሰጣቸውን ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ያለችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የመንግስት አስተዳደር እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ነባራዊ ሁኔታን የሚያስገነዝቡ ሃሳቦች በስልጠናው እንደሚሰጡም ገልጸዋል። 

የምክር ቤት አባላትም በሚቀርቡ ጽሑፎች ላይ በሚደረጉ ምክክሮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ስልጠናውን በአጽንኦት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

በስልጠናው የሚቀርቡ ሃሳቦችም በአገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ በመያዝ የጋራ አቋም እንዲፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ የኢትዮጵያ እዳዎችን በመቅረፍ ወደ ምንዳና ሃብት ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ የሚያስችል የሃሳብና የተግባር አንድነት መፍጠርም የስልጠናው ዋና ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል።

በስልጠናው የሚቀርቡ ገንቢ እሳቤዎችም የምክር ቤት አባላት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት ለቀጣይ የድጋፍና ክትትል ስራዎቻቸው መሰረት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

አገራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ የሰላምና ደህንነት፣ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ፣ የጊዜና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም ትኩረት የሚሹ አገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በስልጠናው እንደሚዳሰሱ ተናግረዋል።  

የተዛቡ ትርክቶችን በማስተካከል አሰባሳቢ ትርክትና ብሔራዊ አርበኝነት መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት አፈ-ጉባኤው፤ በስልጠናውም አገራዊ ትርክት መፍጠር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።


 

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ፤ አካዳሚው ከነበረበት ሁኔታ ወጥቶ ብቃት ያለው የስልጠና ማዕከል ለማድረግ የተሰራውን ስኬታማ ስራ አድንቀዋል።

በቀጣይም የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የተቋማት ኃላፊዎችና መሪዎችን ለማብቃትና ተተኪ አመራሮችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል። 

ለዚህም የልህቀት አካዳሚውን በበጀት፣ በሰው ሃይልና በመሰረተ ልማት የተሟላ እንዲሆን የምክር ቤቱ ቀጣይነት ያለው እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የቀድሞው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ፤ አገራዊና ማህበራዊ እዳዎችን ወደ ምንዳ የመቀየር ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

ለዚህም የተሰጡ ኃላፊነቶችን በብቃት በመወጣት ቀጣይነት ላለው የተቋም ግንባታ በትኩረት መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም