ቀጥታ፡

በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን ዝናብ በሳይንሳዊ መንገድ በማቆር ለልማት ማዋል እንደሚገባ ተገለፀ

አዳማ፤ ጥቅምት 18/2016 (ኢዜአ )፦ በ አርብቶ አደሩ አካባቢዎች  እየጣለ ያለውን ዝናብ ውሃ በባህላዊና በሳይንሳዊ መንገድ በማቆር ለመስኖ ልማት ማዋል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለፁ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍን ወደ ክልሎች ለማውረድ በተዘጋጀ መድረክ ላይ  ነው።

በአሁኑ ወቅት በምስራቅ፣ ደቡብ ምስራቅና በደቡብ ኢትዮጵያ ዝናብ እየጣለ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ በተለይ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ዝናብ እያገኙ ናቸው ብለዋል።

በዚህም የቦረና፣ የምስራቅ ቦረና፣ የጉጂ፣ የደቡብና የሶማሌ ክልል ዞኖች፣ ባሌና ምስራቅ ሐረርጌ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች የበጋ ወቅት ዝናብ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል ።

አካባቢዎቹ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ በድርቅ መጎዳታቸውን የገለፁት ዶክተር ሀብታሙ ''አሁን እየጣለ ያለውን የዝናብ ውሃ በባህላዊና በሳይንሳዊ መንገድ በማቆር ለሰብልና ለእንስሳት መኖ ልማት ማዋል አለብን'' ነው ያሉት ።

ባለፈው ዓመት የነበረው ድርቅ የቤት እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርሱም የአየር ጠባይ ትንበያና ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ የሰው ህይወትን ለመታደግ መቻሉን ተናግረዋል።


 

በወቅቱ ከደረሰው ችግር በመማር በቦረና፣ በባሌ፣ በምስራቅና ምዕረብ ሐረርጌ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ግድቦች መገንባታቸውን የገለፁት ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ''ግድቦቹ በተገቢው መንገድ የዝናብ ውሃ እንዲይዙ ማድረግ አሁን ዋና ሥራችን መሆን አለበት'' ብለዋል።

በተጨማሪም አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በባህላዊ መንገድ የዝናብ ውሃን በማቆር ለእንስሳት መኖና ለሰብል ልማት በማዋል ከችግሩ በዘላቂነት ለማላቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባው አመልክተዋል።

የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እየሰጠ ያለውን አሁናዊ የአየር ጠባይና የዝናብ ሁኔታ መረጃን በየደረጃው ያለው መንግስታዊ አደረጃጀትና ባለድርሻ አካላት በመውሰድ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባቸውም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ድርቅ በነበረበት ና ደጋማ የሀገሪቷ አካባቢዎች ዝናብ እየጣለ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የበጋ ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች በመደበኛና በመስኖ የሰብልና የእንስሳት መኖ ልማት በትኩረት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዚህም በደቡብ ምስራቅ፣ በምስራቅና በደቡብ የሀገሪቱ አርብቶ አደር አካባቢዎች አመች የሆነ ዝናባማ የአየር ጠባይ ለሚቀጥሉት ወራት እንደሚኖር አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም