የግሎባል ጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ ማቆያና የትምህርት ማእከል በኢትዮጵያ ለመመስረት የተደረሰው ውሳኔ ታሪካዊና ትክክለኛ ነው-አምባሳደር ተፈሪ መለሰ - ኢዜአ አማርኛ
የግሎባል ጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ ማቆያና የትምህርት ማእከል በኢትዮጵያ ለመመስረት የተደረሰው ውሳኔ ታሪካዊና ትክክለኛ ነው-አምባሳደር ተፈሪ መለሰ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2016 (ኢዜአ) ፡- የግሎባል ጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ ማቆያና የትምህርት ማእከል ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል ቀንዲል በሆነችው ኢትዮጵያ ለመመስረት የተደረሰው ውሳኔ ታሪካዊና ትክክለኛ ነው ሲሉ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ገለጹ።
የግሎባል ጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ ማቆያና የትምህርት ማእከል በኢትዮጵያ መንግስት ህጋዊ አውቅና ማግኘቱም ተገልጿል።
የማዕከሉ ዕውቅና ማግኘት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን እና በመላው አለም ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች የላቀ ታሪካዊ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት በዩናይትድ ኪንግደምና በመላው አለም የሚገኙ አፍሪካውያንና ሌሎች ጥቁር ህዝቦች በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሲያካሂዱት የነበረው ምክክር በኢትዮጵያ የግሎባል ጥቁር ህዝቦች የታሪክ፣ የቅርስ ማቆያና የትምህርት ማእከል ለመገንባት ሙሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡
ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የማእከሉ መስራች አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት በተካሄደ ውይይት አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ማእከሉን ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል ቀንዲል በሆነቸው ኢትዮጵያ ለመመስረት የተደረሰው ውሳኔ ታሪካዊና ትክክለኛ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም የጥቁር ህዝቦች ታሪክ ሰፊና ጥልቅ ቢሆንም እስከ አሁን ወጥ በሆነ ተቋም ተደራጅቶ ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ በቂ ስራ እንዳልተሰራ መግለጻቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ኢትዮጵያ በየዘመኑ ለአፍሪካ ህዝቦች ነጻነት ትግል ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰው አሁንም የግሎባል ጥቁር ህዝቦች ታሪክና ቅርስ ማቆያ ማእከልን ለመክፈት ለተደረሰው ውሳኔ ህጋዊ በማድረግ ተግባራዊ ምላሽ ሰጥታለች ብለዋል፡፡
የሰው ልጅ ጥንታዊ መገኛ፣ ለአለም ቅርስና ታሪክ አስተዋጽኦ ሚናዋ ከፍ ያለ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በሆነቸው ኢትዮጵያ ማእከሉ መመስረቱ ለአዲሱ ትውልድ የነጻነት፣ ችግርን የመቋቋምና በአንድነት አቅምን የማሳደግ ስልትን በተመለከተ ግንዛቤ መፍጠሪያ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ማእከሉ ለመላው የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የምርምር ተቋም፣ ትውልዶች ሊማሩባቸው የሚችሉ ቅርሶች ማሳያ፣ የቀደሙት የነጻነት ታጋዮች ቁርጠኝነት እንዲሁም ያሳለፏቸውን ታሪኮች መነሻ በማድረግ አዲሱ ትውልድ አንድነትን እና ጽናትን የሚማርባቸው እንዲሆን ተደርጎ ይቀረጻል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ላለፉት ለሶስት አመታት በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመገኘት ለማእከሉ ምስረታ ሲሟገቱ ለነበሩ ከፍተኛ ምሁራንና ሌሎች አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጥቁር ህዝቦች ታሪክ ስፔሻሊስትና ደራሲ ሮቢን ዎከር በበኩላቸው ከድህረ ቅኝ አገዛዝ በኋላ በጥቁር ህዝቦች ላይ ያተኮረው ትርክት የተዛባና የበታችነት ስሜት እንዲጎለብት የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት ጥቁር ምሁራን በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት በራስ መተማመን ላይ የተመሰረተ ስነ-ልቦና መላበስ ለጥቁር ህዝቦች ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህን ስነ-ልቡና ለማጎልበት ቅድመ ቅኝ አገዛዝ የጥቁር ህዝቦችን ታሪክና ቅርስ መመርመር የሚያስችል ማእከል አዲስ አበባ ላይ መመስረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለማእከሉ ህጋዊ እውቅና መስጠቱና በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መድረኩን ከማመቻቸት ጀምሮ እንደ አንድ የግሎባል ጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ ማቆያና የትምህርት ማእከል አካል ሆኖ መስመር በማስያዝ በኩል ለተጫወቱት ሚና አመስግነዋል፡፡
የቡድኑ አስተባባሪ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ጸጋዬ ጫማ በበኩላቸው ቡድኑ የማእከሉን ምስረታ ለማቀላጠፍ ወደ አዲስ አበባ መጓዙን እና ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
በመጪው ታህሳስ በአፍሪካ ህብረት የህብረቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ስራውን በይፋ እንደሚጀምርም ገልጸዋል፡፡