ቀጥታ፡

ያለማንም ጣልቃ ገብነት እስከ አሁን በሰባት ክልሎች በወረዳ ደረጃ ወኪሎች ተመርጠዋል - የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2016(ኢዜአ)፦ ያለማንም ጣልቃ ገብነት እስከ አሁን በሰባት ክልሎች በወረዳ ደረጃ ወኪሎች መመረጣቸውን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ "የሚዲያ ሚና ለአገራዊ ምክክርና አገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ሥልጠና እየሰጠ ነው።

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በመፍታት አገራዊ መግባባት ለመፍጠር፤ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/14 ተቋቁሟል።

ኮሚሽኑ አሳታፊና አካታች አገራዊ ምክክር ለማድረግ እየሰራ ነው፤ በሰባት ክልሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በተሳካ ሁኔታ ሰርቷል።

ሚዲያዎች የአገራዊ ምክክር አስፈላጊነትና ዓላማና ለአገር የሚያስገኘውን ሁለተናዊ ጥቅም በሁሉም ቋንቋዎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ የማይተካ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገልጸዋል።

አካታችነት የአገራዊ ምክክር መርሆ ነው ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምንና መግባባትን ለማምጣት በሃይል ብዙ ተሞክሯል ነገር ግን አተልሳካም፤ ከዚህ መነሻነት ችግሮችን በምክክር መፍታቱ ተመራጭ አማራጭ ሁኗል ብለዋል።




 

ይህን የዘላቂ ሰላም መንገድን ተከትሎ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የአገራዊ ምክክር ዓላማዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ሚዲያዎች የማይተካ ሚና ስላላቸው በትኩረት መስራት እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሚዲያ መሪዎች በበኩላቸው የተጀመረውን የአገራዊ ምክክር ሒደት ውጤታማ ለማድረግ አዳዲስ ይዘቶችን በመጨመር በቁርጠኝነት እየሰራን ነው ብለዋል።

በዘላቂነት ችግሮች መፍታት የሚቻለው በውይይትና በምክክር እንጂ በአፈሙዝ አለመሆኑን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

በሥልጠናው ላይ ስለ አገራዊ ምክክር ጽንሰ ሃሳብ፣ የሌሎች አገራት ተሞክሮዎች፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሕግ ለማቋቋም ያስገደዱ ገፊ ምክንያቶችና የአዋጁ መንፈስ፣ የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ አሰባሰብና የምክክር ሂደቱ ጉዳዮችን የተመለከቱ የውይይት መነሻዎች መቅረባቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም