ክልሎችና ባለሀብቶች ለአዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማጠናከሪያ 400 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አደረጉ

ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 17 /2016 (ኢዜአ)፡- የተለያዩ ክልሎች፣  ከተማ አስተዳደሮችና ባለሀብቶች ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማጠናከሪያ  400 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ  ድጋፍ አደረጉ። 

ክልሉን በጋራ ለማልማት እንደሚሰሩም ድጋፍ ሰጪዎቹ አረጋግጠዋል። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ዛሬ በሆሳዕና ከተማ በተከበረበት ወቅት የተሳተፉ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ፤ ክልሉን በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በማጠናከረ  ለሀገራዊ ብልጽግና መረጋገጥ በህብረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት  አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክትም እንደ ሃገር በእኩልነት፣በነጻነትና በወንድማማችነት ስሜት ጠንክሮ መስራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም በትጉዎችና በሚሰሩ እጆች የተደራጀና የበርካታ ተፈጥሮአዊ ሃብቶች ባለቤት እንደሆነ መረዳታቸውን ጠቅሰው፤ ያለውን አቅም በመጠቀም ክልሉን በጋራ ለማልማት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ክልሉን ለማጠናከር የሚያግዝ  100 ሚሊዮን ብር በክልሉ ስም ድጋፍ አድርገዋል።

''የወደፊት እጣፈንታችን በአንድ ላይ የተገመደ ነው፤ 'የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጋራ መፍታት ይገባናል'' ብለዋል አቶ ሽመልስ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤  ክልሉ የለውጡ መንግስት ለህዝቡ አደረጃጀት ጥያቄ በሰጠው ፈጣን ምላሽ መመስረቱን ጠቅሰው፤ ፈጥኖ ወደ ልማት በመግባት የተሻለ እድገት እንደሚያስመዘግብ   እምነታቸው መሆኑን  ገልጸዋል። 


 

አደረጃጀት በራሱ ግብ ባለመሆኑ ለህዝቡ ተጠቃሚነትና ብልጽግና መረጋገጥ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

የህዝቡን የመልካም አስተዳደር፣የመልማትና በጋራ ሰርቶ የመበልጸግ ፍላጎት ለመመለስ የተገኘውን እድል በተገቢው መጠቀምና ለሃገር ልእልና በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግም ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ከንቲባዋ በከተማ አስተዳደሩ ስም ለአዲሱ ክልል ማጠናከሪያ  የ60 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የክልሉ አደረጃጀት በቀድሞ ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሲነሳ የነበረው  ጥያቄ ሰላማዊ  መንገድ የቀረበ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ ናቸው።


 

የተፈጠረውን አዲስ አደረጃጀት በመጠቀም የአካባቢውን የመልማት አቅም ህዝቡን በማስተባበር ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባትና የህዝብ ትስስር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባል ብለዋል  አቶ አረጋ።

የአማራ ክልል መንግስት ክልሉን  ለማገዝ 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ይፋ አድርገዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፤ በክልሉ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ እንዳለ መረዳታቸውን ገልጸዋል። 

የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች አንድነትና አብሮነት  በማጠናከር የጋራ ሃገር ለመገንባት  የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ  አረጋግጠዋል፡፡

በታታሪ ህዝቦች የተገነባው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በልማት ቀዳሚ በመሆን ለሃገር ምሳሌ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በክልሉ መንግስት ስም የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፤ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች በጋራ የተገነባ እሴት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጋራ የተገነቡት እሴቶችም የሚያስተሳስሩ፣ አብሮነትን፣አንድነትና ወንድማማችነት የሚያጠናክሩና የጋራ ሃገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ መሆናቸውንም  አመልክተዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የሌሎች ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድርና ከንቲባዎች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች 300 ሚሊዮን ብር የሚጠጋና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለሃብቶች  ደግሞ 100 ሚሊዮን ብር  ድጋፍ አድርገዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም