ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በትምህርት ዘርፍ የተያዙትን ግቦች ለማሳካት እያገዘ መሆኑን ገለጸ

ጅግጅጋ  ፤ ጥቅምት 17 /2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር  የአባላትን መብትና ጥቅም ከማስከበር በተጓዳኝ በትምህርት ዘርፍ የተያዙትን ግቦች ለማሳካት እያገዘ  መሆኑን  ገለጸ።

ማህበሩ 36ኛ መደበኛ የምክር ቤት ጉባኤውን  ዛሬ በጅግጅጋ ማካሄድ ጀምሯል። 


 

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በጉባዔው ላይ እንደተናገሩት፤  ማህበሩ የአባላቱን ጥቅም የሚያስጠብቁ ተግባራትን እያከናወነ ነው፤ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማምጣትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር  እየሰራ ነው።

ከነዚህም ባለፈው ዓመት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራ ክብደት ምዘና ክፍያና የቤት ኪራይ ድጎማ የሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ጥናት ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የመምህራን  የመብት፣የጥቅማ ጥቅምና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች መፍትሄ እንዲያገኙ ከፌዴራልና ከክልል አግባብ ያላቸው አካላት ጋር መወያየቱን ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሀገር ደረጃ የተያዙ የትምህርት ዘርፍን  የሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ እየተሳተፈ መሆኑን አመልክተው፤ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በትምህርት ጥራት ላይ ያተኮሩ ሰባት ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

ጉባኤው  በትምህርት ጥራት፣ በመምህራን መብትና ጥቅማ ጥቅም በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። 

የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱላሂ አብዲ፤  የክልሉ መምህራን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ  እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግና ለማስፋፋት የድርሻቸውን እየተወጡ ናቸው ብለዋል ። 

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የመምህራንን መብትና ጥቅማ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ክልሉ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ኃላፊው አረጋግጠዋል። 

ለሦስት ቀናት የሚቆየው ጉባኤው  የማህበሩ፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፎቹ የ2015 የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተመልክቷል። 

በጉባኤው ላይ የክልሎች፣የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር መምህራን ማህበር እንዲሁም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበራት አመራር አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም