ቀጥታ፡

የጋምቤላ ክልል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩ  የክልሉ መንግሥት አሳሰበ

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 17/2016(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የተጀመረውን የብዝሃ ልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ለማገዝ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ብቁ  የሰው ኃይል የማፍራት  ተግባራቸውን  እንዲያጠናክሩ የክልሉ መንግሥት አሳሰበ፡፡ 

የጋምቤላ ኦፔኖ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በደረጃ ሶስትና አራት በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 265 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ቾል ኩን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ፤ ከግብርና  ወደ ኢንዱስትሪ መር ለሚደረገው ሽግግር በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው።

በተለይም አሁን ላይ እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር ለተጀመረው የብዝሃ ልማትና የብልጽግና ጉዞ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሰልጥነው የሚወጡ ባለሙያዎችን ማበራከት እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

በክልሉ የተጀመረውን የብዝሃ ልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ለማገዝ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ብቃት ያለው  የሰው ኃይል የማፍራት  ተግባራቸውን  እንዲያጠናክሩ  አቶ ቾል  አሳስበዋል።

ተመራቂዎችም በንድፈ ሃሳብና በተግባር በቀሰሙት ዕውቀት ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲለውጡም አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ሃሐሓሓኃሀሀሀሀገገላፊ አቶ ሰናይ አኩዎር በበኩላቸው፤  ኮሌጁ በክልሉ በመካከለኛ ደረጃ የነበረውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት በመሙላት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች በሰለጠኑባቸው ዘርፎች በመሥራት ለክልሉ ብሎም ለአገሪቱ የብልጽግና ጉዞ እውን መሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። 

የጋምቤላ ኦፔኖ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አብርሃም ማይክል ፤ኮሌጁ መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የስልጠና መስኮች ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮሌጁ ዛሬ በስድስት የሙያ ዘርፎች በደረጃ ሶስትና አራት አሰልጥኖ ካስመረቃቸው  265 ተማሪዎች  132ቱ ሴቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ተመራቂዎቹ  ከሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች መካከል ሒሳብ አስተዳደር፣ ግንባታ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ውሃ ሥራዎች ይገኙበታል ብለዋል።

ከተመራቂዎች መካከል ተማሪ ኡሞድ አጂባ ፤  በሰጠው አስተያት በኮሌጁ በነበረው ቆይታ በንድፈ ሃሳብና በተግባር በቀሰመው ዕውቀት ሥራ በመፍጠር ራሱን   አካባቢውን ለመለወጥ እንደሚጥር ገልጿል፡፡

የጋምቤላ ኦፔኖ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ላለፉት 14 ዓመታት የዛሬዎቹን  ጨምሮ 13 ሺህ 660 ሰልጣኞችን ማስመረቁን ከኮሌጁ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም