የአምራች ኢንዱስትሪውን የመሰረተ ልማትና የግብዓት ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪውን የመሰረተ ልማትና የግብዓት ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2016(ኢዜአ)፦ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚነሱትን የግብዓትና የመሰረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአምራች ኢንዱስትሪው የሚገጥሙ የግብዓት አቅርቦትና የመሰረተ ልማት ግንባታ ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችል ውይይት ከአምራቾች ጋር አካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሃሰን ሙሃመድ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን የልማት ዕቅድ ለማሳካት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የአገርን ኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር አገሪቱ ለምታደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለውም ነው የገለጹት።
ሚኒስቴሩ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል፤ በተለይም ለግሉ ዘርፍ የሚያደርገውን ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
አምራች ኢንዱስትሪውን ከግብዓት አቅርቦትና ከመሰረተ ልማት ግንባታ አንጻር ያለውን ማነቆ ለመፍታት ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት የግሉን ዘርፍ የሚያጋጥመውን ችግሮች ለመፍታት ከምንጊዜም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን አንስተው ለአብነትም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በርካታ ተግዳሮቶች መፍትሄ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የግሉ ሴክተርም በራሱ አቅም መፍታት የሚችለውን ችግሮች መፍታት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ከግብዓትና ከመሰረተ ልማት አንጻር በሚገጥሟቸው ማነቆዎች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሱ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በቅርበት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚከሰቱ የግብዓት አቅርቦትና የመሰረተ ልማት ተግዳሮቶች በዘርፉ ያለውን አቅም አሟጦ እንዳይጠቀም ያደርገዋል ነው ያሉት።
ለዚህም ከግብዓት አንጻር የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የግሉ ዘርፍ ከአርሶ አደሩ ጋር በቅርበት መሥራትና አርሶ አደሩን መደገፍ እንዳለበት ገልጸዋል።
ከመሰረተ ልማት አንጻር ለሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የግሉ ሴክተር የበኩሉን መጫወት እንዳለበት በጥናቱ መጠቀሱን ተናግረዋል።
የቅመማቅማም ዘርፉን በመወከል በውይይቱ የተሳተፉት ተመስገን ረጠቦ በጥናቱ የተጠቀሱት ምክረ ሃሳቦች ወደ መሬት ወርደው ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል ብለዋል።
የቅመማ ቅመም ሴክተሩ ከፍተኛ ውጪ ምንዛሪን የሚያስገኝ ሴክተር መሆኑ ታምኖበት በቅርበት ሊደገፍ እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
በውይይት መድረኩ የአምራቹ ዘርፍ ያለውን አቅም እንዳይጠቀም የሚያደርጉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።