የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዘንድሮ ከ427 ሺህ በላይ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ለመሰብሰብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዘንድሮ ከ427 ሺህ በላይ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ለመሰብሰብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ
አዳማ፤ ጥቅምት 17 / 2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዘንድሮ ከ427ሺህ በላይ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ።
አገልግሎቱ የዘንድሮውን የደም አሰባሰብ ዕቅድ ለማሳካት እንዲያግዘው ከአዲስ አበባ የመምህራን ፎረም ጋር በአዳማ ከተማ እየመከረ ይገኛል።
በዚህ ወቅት የኢትያጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ፤ በተደራጀ መልኩ የደም ልገሳ አገልግሎት ከሚገኝባቸው ተቋማት ትምህርት ቤቶች ቀዳሚ ናቸው ብለዋል።
ባለፈው የበጀት ዓመት በሀገሪቱ ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ከተሰበሰበው ከ375 ሺህ በላይ ዩኒት ደም ውስጥ ከ50 በመቶ የሚበልጠው ከትምህርት ቤቶች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮም በተመሳሳይ ከ427ሺህ በላይ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ዕቅዳችንን ለማሳካት ከመምህራን ፎረም ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።
ከታቀደው ውስጥ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 75ሺ700 ዩኒት ደም መሰብሰቡን አመልክተዋል።
በአዳማ የተዘጋጀው መድረክም የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን ፣ተማሪዎችና መምህራን በትምህርት ተቋማት የሚያደርጉትን የደም ልገሳ ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ለማመቻቸት እንደሆኑ ተናግረዋል።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ትምህርት ቤቶች በደም ልገሳው ሂደት የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሳፉሪ አካዳሚ መምህር አቶ ዳግማዊ ታምራት ፤ አካዳሚው ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት እየተንቀሳቀሰባቸው ካሉት መካከል ተማሪዎቻቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያደረጉት ያለው ተሳትፎ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
በዚህም ደም በበጎ ፈቃድ በመሰብሰብ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዕውቀት ለፍሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው፤ እኛ በምንለግሰው ደም ብዙ እናቶች ህይወት ይታደጋል ብለዋል።
ዘንድሮ በትምህርት ቤቱ ካሉት 1ሺህ 400 ተማሪዎች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ደም እንዲለግሱ በተማሪዎች ክበባት ጭምር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትያጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በተለያዩ ተቋማት ግንዛቤ በመፍጠር ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች የሚሰበስበውን ደም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለታካሚዎች በማድረስ የሰውን ህይወትን መታደግ ተልዕኮ ያደረገ ሰብአዊ የመንግስት ተቋም ነው።