ቀጥታ፡

ተማሪዎች የፈጠራ ችሎታቸውን ለማጎልበት የሚያስችላቸው ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 17/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተማሪዎች የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።  

አካዳሚው በ2015 ዓ.ም ክረምት ወቅት ለሁለት ወራት በኤሌክትሮኒክስና በኮምፒዩተር ሳይንስ ሥልጠና ለሰጣቸው 46 የፈጠራ ችሎታ ላላቸው ተማሪዎች ዛሬ የእውቅና መርኃ ግብር አካሄዷል።

ተማሪዎቹ ከ10 ትምህርት ቤቶች የተወጣጡና በ16 የተለያዩ ዘርፎች ሥልጠና መከታተላቸው ተገልጿል።


 

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ጥበበ ሥላሴ ሥዩም አካዳሚው የፈጠራ ሥራን የማበረታታት ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል። 

ይህንንም ተከትሎ በየዓመቱ በክረምት ወቅት የፈጠራ ክህሎትና ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎችን በመመልመል በንድፈ ኃሳብና በተግባር የተደገፈ የአጭር ጊዜ ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በዚህም መሰረት በ2015 ክረምት ወቅት ለሁለት ወራት ሥልጠና የተከታተሉ ተማሪዎች ሥልጠናውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ መቻላቸውን ገልጸው መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። 

አካዳሚው እውቅና የተሰጣቸው ተማሪዎች በቀጣይም የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ ለማስቻል  የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረግላቸው ምክትል ሥራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም