ቀጥታ፡

ኢዜአን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን በኃላፊነት ያገለገሉት የአቶ በቀለ ሙለታ ሥርዓተ-ቀብር ተፈጸመ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 17/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን ለበርካታ ዓመታት በኃላፊነት ያገለገሉት የአቶ በቀለ ሙለታ ሥርዓተ-ቀብር በሰዓሊተ ምህረት ቤተ-ክርስቲያን ዛሬ ተፈጽሟል።

በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ተገኝተዋል።

አቶ በቀለ ሙለታ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሐሙስ ለሊት ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአቶ በቀለ ሙለታ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለጸ ለቤተሰባቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቶ በቀለ ሙለታ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያሳየው፤ አቶ በቀለ ሙለታ ከአባታቸው አቶ ሙለታ ቶላና ከእናታቸው ወይዘሮ ወርቄ ዓለሙ በ1963 ዓ.ም ነበር በአዲስ አበባ የተወለዱት።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወሰን ሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሊድስታር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ወስደዋል።

አቶ በቀለ ሙለታ በሥራ ሕይወታቸው፤ በኢህአዴግ ምክር ቤት ጽኅፈት ቤት ይዘጋጁ በነበሩ የተለያዩ ሕትመቶች ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሰርተዋል።

በመቀጠልም በዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን በተለያዩ ክፍሎች ኃላፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ከዚያ በኋላም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና አዲስ ሚዲያ ኔትወርክንም በኃላፊነት አገልግለዋል።

አቶ በቀለ ሙለታ ባለትዳርና የአንድ ወንድና የሦስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።

Like

Comment

Share

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም