የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋም ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍን መተግበር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋም ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍን መተግበር ይገባል

አዳማ ፤ ጥቅምት 17/2016 (ኢዜአ)፡- የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችል ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍን በየደረጃው ባለ መዋቅር በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢታፋ አስገነዘቡ።
የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍን ለማፅደቅና ወደ ክልሎች በማውረድ ተፈፃሚ ለማድረግ ያለመ የሁሉም ክልሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢታፋ እንደገለፁት በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምክንያት ድርቅና ጎርፍ በተደጋጋሚ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በሀገሪቱ፣ አንዳንድ አካባቢዎች ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ አሁንም ድረስ ድርቅና ጎርፍ በእንስሳትና ሰብል ልማት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋም ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።
በዚህም ማዕቀፉ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ባሉ የአየር ጠባይ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሚተገበር መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ግብርና ፣ ውሃ፣ ጤና፣ ትምህርትና የእንስሳት ሀብት፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መተግበር አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ጠባይ መረጃን በጥራት መሰብሰብ ፣ መተንተን ፣ ማደራጀትና ማሰራጨት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የአገልግሎት ማዕቀፉ በተለይ ጎርፍና ድርቅን ጨምሮ ወቅቱን ባልጠበቀው ዝናብ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ከተፈጥሮ ዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ የሚደረገው የመስኖ ልማት ስራ ስኬታማ እንዲሆን የዝናብ ውሃን ጨምሮ የገፀ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ በአግባቡ እንዲለማ የሚያስችል ግብዓትና መረጃ የሚገኝበት የአሰራር ስርዓት መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለፁት ኢንስቲትዩቱ ሀገሪቷ እያከናወነች ያለችውን ልማትና ዕድገት ማገዝ የሚችል የአየር ጠባይ ትንበያ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍን ፣ ከአየር ጠባይ ትንበያ አገልግሎት ጋር በጋራ የአሰራር ስርዓቱን በውጤታማነት ለመተግበር ነው ብለዋል።
የአየር ጠባይ አገልግሎት ተጠቃሚዎችም ሳይንሳዊ የሆነ ጥራት ያለው የአየር ጠባይ መረጃ ተደራሽ ለማድረግም የአሰራር ስርአት ማእቀፍ ማስፈለጉንም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣ከፌዴራልና ክልል ግብርና ሴክተሮች፣ከክልሎች አካባቢ ጥበቃና ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽኖች የተወጣጡ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆኖዋል።