ቀጥታ፡

ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እቅድ መሳካት የመገናኛ ብዙኃን ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 17/2016 (ኢዜአ)፦ለአገራዊ ምክክሩ እቅድ መሳካት የመገናኛ ብዙኃን ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠየቀ። 

"የሚዲያ ሚና ለአገራዊ ምክክርና ብሔራዊ መግባባት" በሚል መሪ ኃሳብ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ አየተካሄደ ነው። 

በመድረኩ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች፣ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። 

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ከዝግጅት እስከ ተሳታፊ ልየታ የተሳካ ሥራ አከናውኗል ብለዋል። 

ከዝግጅት ምዕራፍ በመነሳት በርካታ ሥራዎችን በማሳካት ሁለተኛውን ምዕራፍ ደግሞ በማገባደድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለምክክር ሂደቱ ስኬት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በእስካሁኑ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመሥራት የተሳካ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የኮሚሽኑን ሥራዎች ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ የሚዲያዎች ሚና የላቀ በመሆኑ እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች ላይ አዎንታዊ ሚና ለተጫወቱ መገናኛ ብዙኃን ምስጋና በማቅረብ ቀጣይ ትብብራቸውን እንዲያስቀጥሉም ጠይቀዋል።

ለምክክር ሂደቱ መሳካት የሰላም ጉዳይ መሰረታዊ በመሆኑ አጠቃላይ ሕዝቡ የሰላም ዘብ እንዲሆን ጠይቀው በተለይም ሚዲያዎች በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። 

የምክክር ኮሚሽኑ እቅድ ተሳክቶ የሚፈለገው ውጤት እውን እንዲሆን ሚዲያዎች የላቀ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዋና ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል። 

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ የተለያዩ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም