ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈንና የዜጎች ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሙስናን በልዩ ትኩረት መታገል የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 17/2016 (ኢዜአ) ፡- በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈንና የዜጎች ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሙስናን በልዩ ትኩረት መታገል የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ። 

ሙስና በግልና በሕዝብ ተቋማት ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎችና መልኮች የሚፈጸም ወንጀል ነው።

መንግሥት የአገር ደኅንነት ሥጋት የሆነውን ሙስና ለመከላከል ብሔራዊ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ በማቋቋም በተለያዩ ጊዜያቶች እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል።

ለአብነትም በ2015 በጀት ዓመት በሙስና መከላከል ተግባራት ከ 7 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉና 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ካሬ ሜትር መሬት ማስመለስ ተችሏል።

በተያዘው ዓመትም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸው ይታወሳል።

የፌደራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ፤ የጸረ ሙስና ትግሉ ሁሉንም ባለቤት በሚያደርግ መልኩ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ተቋማት በተሰጣቸው ተልዕኮ በዘርፍ በመለየት ሁሉንም በሚያሳትፍ መልኩ ሙስናን የመከላከል ሥራዎች መጀመራቸውን ነው ያስረዱት። 

በዚህም በ25 ዘርፎች የተቋማት የሙስና ችግር ልየታ ጥናት መደረጉንም አመላክተዋል።

ተቋማት በዚሁ ጥናት መሰረት ከሚቀርቡ ምክረ ኃሳቦች በመነሳት የራሳቸውን እቅድ አውጥተው እንዲተገብሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ተቋማት ያለባቸውን የሙስና ተጋላጭነት ተረድተው አስፈላጊውን መፍትሄ በመስጠት ሙስናን የመከላከል አቅማቸውን የሚያሳድግ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

ተቋማት የሙስና መከላከል ሥራውን በባለቤትነት እንዲመሩት የተጀመሩት ሥራዎች በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት። 

ቅንጅታዊ አሰራርን ማስፈን ችግሩን ለመፍታት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ጉዳዩ የሁሉም አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንና እስካሁን በተጀመሩ ሥራዎችም ጠንካራ ቅንጅት እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የትግል ሥልቱም ውጤታማ እንዲሆን በብቃትና በቅንጅት መሥራት አማራጭ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ  መሆኑን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ በየደረጃው ካሉ ተቋማት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም ሕግን በማስከበር በኩልም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉን አቀፍ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ሙስናን መዋጋት ለልማት መፋጠን፣ ለሰላም መረጋገጥ፣ ማኅበራዊ ፍትህ እንዲነግስና ምቹ አገር እንዲኖር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። 

ሙስናን መታገል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የሚጠበቅበትም ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም