በጅግጅጋ ከተማ ለሚከበረው 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጅግጅጋ ከተማ ለሚከበረው 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጀምረዋል

ጅግጅጋ፤ ጥቅምት 16/2016 (ኢዜአ) ፡- በሶማሌ ክልል አዘጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ ለሚከበረው 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጀመራቸውን የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ።
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ኢብራሒም ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዓሉ "ብዝሀነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በቀጣይ ህዳር ወር መጨረሻ በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት ይከበራል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በአቶ ኢብራሒም ኡስማን አስተባባሪነት የሚመራና የክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች እንዲሁም የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት የተካተቱበት ዐቢይ ኮሚቴ መዋቀሩን ምክትል አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።
ለእንግዶች ማረፊያ እና የውይይት መድረክ የሚዘጋጅባቸው ሆቴሎችና የተለያዩ መሰብሰቢያ አዳራሾችን የመለየት ሥራ መከናወኑም አመልክተዋል።
ምክትል አፈ ጉባኤው እንዳሉት በዓሉ ለፌዴራሊዝም ስርዓት መጎልበት ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር በጅግጅጋ ከተማ በመገንባት ላይ ያሉ የመንገድና የውሃ መሰረተ ልማቶችን ለማፋጠን ጠቀሜታው የጎላ ነው።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ ምክር ቤት የመሰብሰቢያና የአስተዳደር ሕንጻዎች ግንባታን ሥራን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በበዓሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚያጎለብቱባቸው የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱም ምክትል አፈጉባኤው ገልጸዋል።
ከአሥር ዓመት በፊት 8ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሶማሌ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ጅግጅጋ ከተማ በድምቀት መከበሩ የሚታወስ ነው።
ባለፈው ዓመትም በዓሉ ለ17ኛ ጊዜ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት በሀገር አቀፍ ደረጃ መከበሩ ይታወቃል።