ቀጥታ፡

በክረምት የነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 16/2016 (ኢዜአ) ፡-በኢትዮጵያ ባሳለፍነው የክረምት ወራት የነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።

የ2015 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ መርኃ ግብር "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ -ሁለት" በሚል መሪ ኃሳብ ተካሂዷል።   

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በ2015 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 21 ሚሊዬን 569 ሺህ ወጣቶች መሳተፋቸው ተገልጿል ።

እነዚህ በጎ ፈቃደኞች በአገር አቀፍ ደረጃ በ13 የሥምሪት መስኮች ተሰማርተው ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎቶች ለሕዝቡ መስጠታቸውንም ነው የገለጹት። 

በክረምት በጎ ፈቃድ ከተሰጠው አገልግሎት ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ፣ የደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ይገኙበታል ብለዋል። 

በክረምት የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች በመንግስትና በማህበረሰቡ ያልተሸፈኑ የሰብዓዊና የልማት ስራዎችን በማከናወን የበኩላቸውን አሻራ ለሀገራቸው እንዲያኖሩ ይሰራል ነው ያሉት።

በተለይ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት አዳዲስ የስምሪት መስኮች በመለየት በክረምት፣ በበጋና በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥለው ለሀገር አኮኖሚያዊ እድገትና ለአንድነት ጉልህ ሚና ስለሚያስገኝ መሆኑን  አክለዋል። 

በዚህም ወጣቱ እምቅ ችሎታውን እንዲጠቀምና ሰብዓዊ ተግባራትን እንዲለማመድ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትር ዴኤታዋ  አብራርተዋል።

በ2015 ዓ.ም በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተሳተፉ ወጣቶች እውቅና ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም