ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የተሰሩ መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላለፉ

ባህር ዳር፤ጥቅምት 16 /2016 (ኢዜአ)፡-  በባህር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች የተገነቡ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላለፉ። 

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  አቶ ጎሹ እንዳላማው በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።


 

ለዚህም በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ 20 መኖሪያ ቤቶች በአዲሰ በመገንባትና 20 ያረጁ ቤቶችን ደግሞ በማደስ ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ የተደረገውን ጠቅሰዋል።

በመንግስትና በባለሃብቶች የተሰሩት  ቤቶቹ  በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የከተማውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።


 

በራሳቸው አቅም ቤት መስራት ለሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን የቤት መስሪያ ቦታ የማቅረብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ ሰላሙን አፅንቶ ለማስቀጠል ከፀጥታ አካሉ ጎን በመሆን የበኩሉን እንዲወጣም አቶ ጎሹ አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በፍቅሩ ብዙ በበኩላቸው፤ 40 በአዲስ የተገነቡና ያረጁ ቤቶችን በመጠገን ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል።


 

ለቤቶቹ ስራ  12 ሚሊዮን ብር ወጪ ከተደረገው ውስጥ 10 ሚሊዬኑ ከመንግስት በጀት ሲሆን ቀሪው  ደግሞ በባለሃብቶች  ድጋፍ የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል።

ቤት የተሰጣቸው ወይዘሮ ትግስት ምስጋናው የእድሉ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የዕድሉ ተጠቃሚ ወይዘሮ አዲሴ ፀጋ ፤ ባለፉት 27 ዓመታት በቤት ኪራይ ውጣ ውረድ እንደደረሰባቸው አውስተው፤  ዛሬ የቤት ችግራቸው በመፈታቱና ለዚህም ድጋፍ ላደረጉላቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም