ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት የሳይበር ምህዳሩን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሚችሉ ወጣቶችን እያፈራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት የሳይበር ምህዳሩን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሚችሉ ወጣቶችን እያፈራች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት የሳይበር ምህዳሩን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሚችሉ ወጣቶችን እያፈራች መሆኑ ተገለጸ።
በዓለም ላይ እንደ ተፈጥሮ አደጋ፣ ወረርሽኝ፣ ግጭትና መፈናቀል ያሉ የሰው ልጆች ስጋት ከሆኑ አስር ጉዳዮች መካከል የሳይበር ጥቃት አንዱ ሆኗል፡፡
የሳይበር ምህዳር የሰው ልጆችን ሥራ በማቀላጠፍና አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የላቀ ሚና ያለው ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የፋይናንስ፣ የደህንት ተቋማት ብሎም የአገራት ሉዓላዊነት ስጋት መሆኑ አልቀረም፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጣር በ2023 ዓለም በሳይበር ጥቃት ምክንያት 8 ትሪሊዬን ዶላር ኪሳራ ገጥሟታል፤ ይህ አሀዝ በ2025 ወደ 10 ነጥብ 5 ትሪሊዬን ከፍ ሊል ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሳይበር ጥቃት ከየትና መቼ፤ በምን ሁኔታ እንደሚፈጠር የማይታወቅ ውስብስብና ዓይነተ ብዙ የደህንነት ስጋት ነው፡፡
ለአብነት ኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም ከተሰነዘረ 214 የሳይበር ጥቃት፤ አይነቱና መጠኑ ጨምሮ በ2014 ዓ.ም ወደ 8 ሺህ 845 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
ተቋማት በሳይበር ምህዳር ያላቸው የሰው ሀይል ብቃት፤ የቴክኖሎጂ አቅም እና የተቋማዊ አደረጃጀት ዘርፉ ከሚፈልገው ከ20 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የነገው ትውልድ የሀገር ሉዓላዊነትና ደህንነት ማስጠበቂያ ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማት በሳይበር ምህዳር ላይ ያላቸውን የሰው ሀይልና የቴክኖሎጂ አቅም ማዳበር አለባቸው ብለዋል፡፡
አስተዳደሩ የሀገሪቱን የሳይበር ሀይል ለማሳደግ ውስጣዊ አቅሙን ከማጎልበት ባሻገር በሀገራዊው የሳይበር ታለንት ማዕከል አማካኝነት ወጣቶችን በማሰልጠንና በማብቃት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት የክረምት መርሃ ግብር ከአንድ ሺህ 500 በላይ ወጣቶች መካከል 62 ወጣቶች የተለያዩ ደረጃዎችን አልፈው ከ26 በላይ ቴክኖሎጂዎችን አልምተዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ወጣቶቹ በጋራ በመሆን ሥራ ላይ መዋል የሚችሉ 14 ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ላይ ናቸው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ የአስተዳደሩ የሳይበር ወታደር ሆነው እያገለገሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው የ2016 በጀት ዓመት በሀገራዊ የሳይበር ታለንት ማዕከል ለክረምት ትምህርት 5 ሺህ 600 ወጣቶች አመልክተዋል ብለዋል፡፡
ከፍተኛ ፉክክር በሚታይበት በዚህ የሳይበር ምህዳር ውድድር ላይ 150 የሚሆኑት ወጣቶች የክረምት ትምህርቱን እንዲቀላቀሉ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ወጣቶች ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማቅረብ የሳይበር ደህንነት ጠባቂዎች የነገዋ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስከባሪዎች መሆናቸውን እያሳዩ ነው ብለዋል፡፡